
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በጋራ መሥራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ሰነድ እና የውል ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ተቋማቱ ሁሉን አቀፍ የሙያ እና የፋይናንስ አቅሞች፤ የሚዲያ፣ የስቱዲዮ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እና ልውውጥ እንዲሁም
ለተሻለ ሀገራዊ ዕድገት መጎልበት በጋራ እንደሚሠሩ በስምምነቱ ተቀምጧል፡፡
የሚጠበቁበትን ፈጣን መረጃዎች በማቅረብ በኩል ተባባሪ በመኾን በአሚኮ ድረ-ገጽ እና ማኅበራዊ ገጾች ላይ እንዲታተሙ እና ሌሎች ተግባራትን እንደሚወጣም በስምምነቱ ተቀምጧል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ ከሀረሪ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር በሁሉም የሚዲያ አማራጮቹ እና በሁሉም ቋንቋዎች በጋራ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል።
የሀረሪ ክልል የሥራ ኀላፊዎች የመረጃ ምንጭ እና የአሚኮ ቤተሰብ በመኾን አብራችሁን ስለሠራችሁ ልዩ ክብር አለን ብለዋል።
አሚኮ ባለቤቱ የአማራ ሕዝብ ቢኾንም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያገለግል የሚዲያ ተቋም መኾኑን በሀረሪ ክልል በመገኘት እና በማገልገል አስመስክሯልም ነው ያሉት።
ስምምነቱ በሚዲያ እና በኮሙዩኒኬሽን ሥራ እንደ ቤተሰብ በጋራ ሥንሠራ የነበረውን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል። በሁሉም ቋንቋዎች ከዚህ በፊት ሥንሠራቸው የነበሩ ሥራዎችን በማጠናከር የሀረሪን ገጽታ፤ የቱሪዝም መዳረሻነት፤ አብሮነት እና ጥንታዊነት ለሁሉም የምናሳውቅበት ሥምምነት ነው ብለዋል።
አዲስ ሥራ ለመጀመር ሳይኾን የጀመርናቸውን ሥራዎች ለማጠናከር እና ውጤታማ ለማድረግ ተፈራርመናል ነው ያሉት።
የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሔኖክ ሙሉነህ “ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን” በሚል ድርጅታዊ መርህ የሚታወቀው አሚኮ ለዓመታት በሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ታሪክ ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ አስቀምጧል ብለዋል።
ለሀገር ገጽታ ግንባታ ግንባር ቀደም ኾኖ የሚሠራ ጠንካራ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። አሚኮ በሀረሪ ክልል የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን፤ የአብሮነት እና የመቻቻል እሴቶችን፤ የቱሪዝም ሀብቶችን፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት እንዲደርስ በብዙ ቋንቋ የሚዲያ ሽፋን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በአሚኮ የዘገባ ሽፋን የሀረሪ ክልል ሕዝብ ደስተኛ ነው ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በቀጣይ በይበልጥ ከአሚኮ ጋር ለመሥራት ስምምነት መፈራረሙንም ገልጸዋል። በቀጣይ ሚዲያውን ለመደገፍ የሀረሪ ክልል በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
አሚኮ አሠባሣቢ እና ገዥ ትርክት ላይ በትኩረት የሚሠራ፤ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ የያዘ እና በሁሉም ቋንቋ በመሥራት ቀዳሚ የኾነ ሚዲያ መኾኑንም አንስተዋል።
አሚኮ ከሀገር ባለፈ በአፍሪካ እና በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለመኾን የሚያደርገው ጉዞ ሩቅ አይደለምም ብለዋል።
የተቋማት ኀላፊዎቹ የአሚኮን ተቋም የጎበኙ ሲኾን በግቢ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል።
#አሚኮ #ስምምነት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_29_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
