አረንጓዴው ሀብታችን – ከተራቆተ መሬት እስከ ቢሊዮን ዶላር ገቢ!

10
🌳
🇪🇹 ☕🥑
ደንን ስናስብ አብዛኛውን ጊዜ ወደ አዕምሯችን ቀድሞ የሚመጣው የአካባቢ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት ሚዛን ወይም የተፈጥሮ ውበት ነው።
የዓለማችን የኢኮኖሚ አውድ ሲመረመር ግን ደን ከዚህ እጅግ የላቀ እና ግዙፍ ትርጉም አለው። ለአብነትም ወደ 70 በመቶ የሚጠጋው የመሬት ስፋቷ በደን የተሸፈነችውን ስዊድንን እንዲሁም ጎረቤቷን ፊንላንድን ብንመለከት ከዓለም አቀፍ ግዙፍ የቴክኖሎጂ እና አውቶሞቢል ኩባንያዎቻቸው ይልቅ የደን ዘርፉ ለኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት ኾኖ እናገኘዋለን።
ኢንዶኔዥያ በደን ሀብቷ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎቿ የሥራ ዕድል ከመፍጠሯም ባሻገር በወጭ ንግድ ገቢዋ ውስጥ ደን ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። እነዚህ ተጨባጭ ማሳያዎች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን ሀቅ ቢኖር የደን ሀብት ከተራ የተፈጥሮ ጥበቃ ጽንሰ-ሀሳብ ባለፈ የሀገራትን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና እና የዜጎችን የኑሮ መሠረት የሚያረጋግጥ የማይተካ የኢኮኖሚ ሞተር መኾኑን ነው።
ይህ ዓለም አቀፋዊ ዕውነታ ለሀገራችን ኢትዮጵያም በተጨባጭ የሚሠራ ነው። የኢትዮጵያ የደን ሀብት ለሕዝቡ የኑሮ መሠረት ከመኾኑም ባሻገር ለአየር ንብረት ቁጥጥር፣ ለውኃ እና ብዝኀ-ሕይወት ጥበቃ፣ ለማኅበራዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ያለው ሚና የላቀ ነው። እ.አ.አ. በ2023 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን “የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት በኢትዮጵያ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት” በሚል ርዕስ የተሠራው ጥናት እንደሚያሳየው ከዚህ ቀደም በየዓመቱ እስከ 72 ሺህ ሄክታር የሚደርስ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ በሥነ-ምኅዳሩ ላይ ከባድ ጫና አሳድሮ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ሀገሪቱ ይህንን ተግዳሮት በመቀልበስ የተራቆቱ መሬቶችን በድጋሚ በማልማት ተስፋ ሰጭ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሰፊ የደን ሀብት ቢኖራትም ዘርፉ ለሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በ2015 እ.አ.አ 2 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ እንደነበር ጥናቱ አስታውሷል። ነገር ግን እ.አ.አ በ2016 የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ባደረገው ጥናት ደን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ወደ 13 በመቶ ከፍ ብሏል። የደኖች ጥቅምም በትክክል ስለማይመዘገብ እና ከሌሎች ዘርፎች ጋር ስለሚካተት እንጂ ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያለው እምቅ አቅም እጅግ ከፍተኛ እንደኾነ ጥናቱ አስምሮበታል።
የዚህ ሀብት ኢኮኖሚያዊ ትርጉም በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይኾን በገጠሩ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥም ይገለጣል። ማኅበረሰቡ እንደ ማገዶ፣ የከብት መኖ፣ ማር፣ ቡና፣ ቅመማ ቅመም እና የመድኃኒት ዕፅዋትን በስፋት ይጠቀማሉ።
የማኅበሩ ጥናት እንደሚያሳየው በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ከ10 እስከ 60 በመቶ የሚኾነውን የዕለት ተዕለት ገቢውን የሚያገኘው ከዚሁ ከደን ሀብት ነው።
የደን ሀብቱን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የደን ዘርፍ ልማት ስትራቴጂዎችን በተግባር እያዋለ ይገኛል። በተለይም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አማካኝነት እየተከናወነ ያለው ዛፍ የመትከል ሥራ አስደናቂ ሀገራዊ ለውጦችን እያመጣም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቅርቡ አረንጓዴ አሻራ የአፈር ለምነትን ከማስጠበቅ አልፎ በቡና እና አቮካዶ ልማት ተጨባጭ የኢኮኖሚ ስኬት አምጥቷል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት ብቻ ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፤ ደን ልማትን መነሻ አድርጎ በተሠራው ሥራም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ ላኪ ሀገር መኾን ችላለች ብለዋል።
ይህም የደን ሀብታችን የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይኾን የኢኮኖሚያችንም ዋነኛ ሞተር መኾኑን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ እንደኾነ ነው የጠቆሙት።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በጤናው ዘርፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል” ዶክተር መቅደስ ዳባ
Next articleየኮሪደር ልማቱ ለባሕር ዳር ከተማ ውበት እና ለቱሪዝም ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ጥሏል።