የኮሪደር ልማቱ ለባሕር ዳር ከተማ ውበት እና ለቱሪዝም ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ጥሏል።

11
🌴
በዓባይ ወንዝ እና በጣና ሐይቅ ውበት በደመቀችው በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ለዓለም አጉልቶ ያሳየ እና ተወዳዳሪነቷን ያሳደገ ትልቅ ስኬትም ነው።
ልማቱ ከተማዋ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለጎብኝዎች ደግሞ ሳቢ እና ማራኪ እንድትኾን ያስቻለ ሲኾን የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከማሻሻል ባለፈ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ጠንካራ መሠረት ጥሏል ብለዋል።
ልማቱ ከጣና ሐይቅ ጋር በተጣመረ መልኩ መከናወኑ ጎብኝዎች ካረፉበት ቦታ በእግር፣ በተሽከርካሪ እንዲሁም በውኃ ትራንስፖርት (በጀልባዎች) በቀላሉ እየተዝናኑ ወደሚፈልጉት መዳረሻ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ፈጥሯል።
በተለይም በልማት ማዕቀፉ ውስጥ የተካተቱት አምፊቲያተሮች፣ ከጀልባ ወደቦች ጋር የተናበቡ መሠረተ ልማቶች፣ ባሕላዊ ኤግዚቢሽኖች እና ፌስቲቫሎች ለቱሪዝም ዕድገቱ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾናቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
አስደናቂው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድም አወንታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በፎቶግራፍ አንሺነት፣ በቲክቶክ እና በሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችገቢ ለማግኘት የሚጥሩ በርካታ ወጣቶች ወደ ከተማዋ እንዲሳቡ በማድረግ ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የመኖሪያ ስበት መፈጠሩም ተጠቅሷል።
በ2018 የበጀት ዓመት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ከታቀደው በላይ ውጤት የተመዘገበ ሲኾን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፍሰት እንዲሁም ከዚሁ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።
ይህ አበረታች ውጤት የባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ማነቃቃቱን እና የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ሁለገብ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መኾኑን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
✍️በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአረንጓዴው ሀብታችን – ከተራቆተ መሬት እስከ ቢሊዮን ዶላር ገቢ!
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናልን መረቁ ።