ፀደይ ባንክ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ተረድቶ ችግር ፈቺ ኾኖ የዘለቀ ባንክ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

27

 

ፀደይ ባንክ ለሦሥት ቀናት ያካሄደውን የ2025/26 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2026/27 ዕቅድ ትውውቅ አድርጓል።

ከሐምሌ 26/2018 ዓ.ም እስክ ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም የተካሄደው የአፈፃፀም ውይይት እና ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ለባንኩ ቀጣይ ሥራዎች ስኬት ወሳኝ መኾኑ ተነግሯል።

በማጠቃለያ መድረኩ ለባንኩ መሥራች እና ለቀድሞ ፕሬዝዳንት መኮንን የለውምወሰን የተሽከርካሪ ሽልማት ተሰጥቷል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የቀድሞው የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ መኮንን የለውምወሰን ላለፉት 30 ዓመታት የፋይናንስ ተቋሙን መርተው ለባንክነት ያበቁት የፀደይ ባንክ ባለውለታ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የባንኩ ሠራተኞች እና ቅርንጫፎችም ዕውቅና ሰጥተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ ዕውቅና መሰጠቱ ሠራተኞችን ይበልጥ የሚያበረታታ እና ለሌሎች ደግሞ የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በተለይም ፀደይ ባንክ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ተረድቶ ችግር ፈቺ ኾኖ የዘለቀ ባንክ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አክለውም ከማይክሮ ፋይናንስ እስከ ባንክ የሄደባቸውን አስቸጋሪ ችግሮች አልፎ እዚህ መድረሱ አስደናቂ ነው ብለዋል።

ፀደይ ባንክ እ.ኤ.አ.በ2040 በአፍሪካ ካሉ 40 ባንኮች ቀዳሚ ለመኾን እየሠራ ያለው ተግባር ዕውን የሚኾነው በሠራተኞቹ ብርታት መኾኑን የተናገሩት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሃንስ አያሌው (ዶ.ር) በዚህ ሳይዘናጉ በትጋት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በሀብት አሠባሠብ፣ በብድር አቅርቦት እና ማስመለስ፣ በውጭ ምንዛሬ ክምችት፣ የባንኩን ጥሬ ገንዘብ በአግባቡ በማሥተዳደር እና በሌሎች መመዘኛዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

በዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምክንያት የፋይናንስ ዘርፍ ተገማች ባልኾነበት በዚህ ወቅት ፀደይ ባንክ በአዲስ የለውጥ አመራር ስር ኾኖ ፈተናዎችን በመቋቋም የበጀት ዓመቱን በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቋል።

በተለይ ደግሞ ባለፉት አምስት ወራት በተተገበሩ ባለሦሥት ተቋማዊ ስትራቴጂካዊ የሪፎርም ዕቅዶች የባንኩ ታሪክ መቀየሩ ተገልጿል።

ባንኩ በቀጣይ ዓመት በተቀማጭ ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ እና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ልቆ ለመገኘት ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ገብቷል።

#AMECO #TsedeyBank #BankingExcellence #FinancialGrowth

#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_29_2018_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሃብቴ ተሻገር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🇪🇹 “ሀገር ከሁሉም በላይ ናት”
Next articleአሚኮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ በትጋት መሥራት ይኖርበታል አቶ ዓባይ መንግሥቴ