አሚኮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ በትጋት መሥራት ይኖርበታል አቶ ዓባይ መንግሥቴ

17
🌍
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በዓመታዊ የአፈጻጸም ውይይትና የቀጣይ ዓመት እቅድ ትውውቅ መርሐ ግብር በኮርፖሬሽኑ ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ ለቆዩ ጡረታ ለወጡ የቀድሞ ሠራተኞች እና በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሠራተኞች ዕውቅና ሰጥቷል።
በዕውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ አባል እና የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ባስተላለፉት መልእክት አሚኮ ባለፉት ዓመታት ለክልሉም ኾነ ለሀገር ሰላም መስፈን፣ ለሕግ መከበር፣ ለልማት መፋጠን እና የሕዝብ አንድነት እንዲጠናከር ላበረከተው አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።
ኮርፖሬሽኑ በመረጃ ቀዳሚ እና በብዙ ቋንቋዎች ተደራሽ በመኾን ዐበይት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ለዚህ ስኬት ዋናው ምስጢር የአመራሩ እና የባለሙያው ተቀናጅቶ፣ ተናቦ እና አቅዶ ያለእረፍት መሥራት እንደኾነም ገልጸዋል። ለስኬቱ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር፣ የካቢኔ አባላት እና የቦርድ መሪዎች ላደረጉት ድጋፍ ዕውቅና ሰጥተዋል።
የአሚኮ ተደራሽነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። በቀጣይም አሚኮ የጀመረውን ዕድገት በማስቀጠል የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ በትጋት መሥራት እንደሚገባውም አመላክተዋል።
አሚኮ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ መሪዎች፣ ሠራተኞች እና ቀደም ሲል ተቋሙን ላገለገሉ ባለሙያዎች ዕውቅና እና ምሥጋና ማበርከቱንም ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በጡረታ የተገለሉት ነባር ባለሙያዎች አሚኮን የሙያ ማሳደጊያ ብቻ ሳይኾን የሕይወት ትምህርት ቤት እና የሁለገብ ስኬት መሠረት አድርገው እንደሚቆጥሩትም ተናግረዋል። በተቋሙ ውስጥ ባሳለፏቸው ረጅም ዓመታት ያጋጠሟቸውን ውጣ ውረዶች ወደ ስኬት በመቀየር፣ ከተራ ባለሙያነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት መድረስ መቻላቸውን እና ቤተሰባቸውን በክብር ማሳደጋቸውን አስታውሰዋል።
ከራሳቸው ዕድገት ባሻገር ሠርተው የማይታክቱ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራታቸውን በኩራት በማንሳት ወደፊትም የትም ቦታ ቢኾኑ ይህን ውለታ የዋለላቸውን ተቋም ለማገዝ ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleፀደይ ባንክ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ተረድቶ ችግር ፈቺ ኾኖ የዘለቀ ባንክ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየተሰበረው የካይሮ ሕልም እና አይበገሬው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት