ከጠመንጃ ፖለቲካ ወደ ሀሳብ የበላይነት

15

 

በኢትዮጵያ ችግሮችን በኃይል እና በጠመንጃ ለመፍታት ለዘመናት ሲደረግ የነበረው ሙከራ ሀገሪቱን ከጦርነት አዙሪት ውጭ ያተረፈላት ነገር አልነበረም። ይህንን አጥፊ የፖለቲካ ባሕል በመቀየር በንግግር እና በምክክር ላይ የተመሠረተ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአራት ዓመታት የዘለቀ እልህ አስጨራሽ የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቅቆ ወደ ዋናው ታሪካዊ ጉባኤ ተሸጋግሯል።

ይህ ሂደት ከኀይል ፖለቲካ ወደ ሰላማዊ ውይይት የሚደረገውን ሀገራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት አዲስ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በኀይል ሥልጣን የመያዝ እንዲሁም አሸናፊ እና ተሸናፊን የሚፈጥር አካሄድ የሰፈነበት ነበር። ሀገራዊ ምክክሩ ግን ይህንን አጥፊ አዙሪት በመስበር የጋራ የአሸናፊነት አስተሳሰብን ለማንበር የተነደፈ ነው። ግጭቶች የሚፈጠሩት በሀሳብ ልዩነት ብቻ ሳይኾን ሀሳብን በነፃነት የሚያስተናግድ እና የሚያስማማ መድረክ በመታጣቱ ጭምር ነው።

በመኾኑም ምክክሩ በዜጎች እና በፖለቲካ ኀይሎች መካከል የታጡ የጋራ እሴቶችን፣ የታሪክ ትረካዎችን እና የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ዕይታዎችን በውይይት በመፍታት የጠመንጃ አፈሙዝ ሳይኾን የሀሳብ የበላይነት የሚነግስበትን አዲስ ባሕል ይገነባል።

የምክክር ሂደቱ ተዓማኒነት እና ቅቡልነት እንዲኖረው ከታች ወደ ላይ የኾነ ስልት ተከተሏል።

የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ እንደሚሉት ሂደቱ በሁሉም ክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደሮች ሰፊ ውይይቶችን በማካሄድ በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 234 ወረዳዎችን ማሳተፍ ችሏል።

ይህም ሂደት ከመላው ሀገሪቱ የተወከሉ ተሳታፊዎችን በአንድ ጠረጴዛ ማሠባሠብ ችሏል። የአጀንዳ ቀረጻ ሂደቱ የዓለም አቀፍ ልምዶችን፣ የጥናት ግኝቶችን እና ሳይንሳዊ ሂደቶችን የተከተለም ነው። የሕዝቡን ቅሬታ፣ ሥጋት፣ ፍላጎት እና ተስፋ መሠረት ያደረጉ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ለዋናው ጉባኤ ለይቷል። እነዚህ አጀንዳዎች በኅብረተሰቡ መካከል እንዲሁም በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሻሻል መተማመን እንዲፈጠር የማድረግ ከፍተኛ አቅም አላቸው።

ጊዜያዊ የሰላም ስምምነቶች ወይም የኀይል እርምጃዎች ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንዳልቻሉ ያለፉት ዓመታት ማሳያዎች ናቸው። ሀገራዊ ምክክሩ ግን ስር የሰደዱ ውስጣዊ ችግሮችን ከሥራቸው በመንቀል ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው መፍትሔ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ይህ ምክክር እንደ ታሪካዊ ዕድል እና ስጦታ የሚወሰድ ሲኾን ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች እና የተረጋጋች ሀገር ለማውረስ ያስችላል። ሁሉም ወገን የተሳተፈበት እና ያመነበት ውሳኔ ላይ መደረሱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖራቸው በማድረግ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መንገድ ይጠርጋል።

በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክር በራሱ ለሁሉም ችግሮች ተዓምራዊ መፍትሔ ባይኾንም፣ የጦርነት ፖለቲካን ለማስቀረት እና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው። የዘመናት ቋጠሮዎችን ፈትቶ አስተማማኝ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ይህ ታሪካዊ ጉዞ ዳር እንዲደርስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በጎ ፍላጎት፣ ቁርጠኝነት እና ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ይኾናል።

#AMECO #ሀገራዊ_ምክክር

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_29_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleምሥራቅ ዕዝ ዞብል ክፍለ ጦር በሰከላ ወረዳ ያሠለጠናቸውን የሰላም አሥከባሪዎች አስመረቀ።
Next article🇪🇹 “ሀገር ከሁሉም በላይ ናት”