የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።

18
​በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ”በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብዓዊነት ማገልገል”በሚል መሪ መልዕክት ሲሰጥ የቆየው የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት ምረቃ ተካሂዷል።
በምረቃ መርሐግብሩ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
​የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎች የሰላም አምባሳደር መኾናቸውን ጠቅሰው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምን ለማስከበር ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሕዝብን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ላይም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
​በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ102ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል እሸቱ መንግሥቴ በበኩላቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለተገኘው ሰላም የጸጥታ ኀይሉ የላቀ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። ለቀጣይ ተልዕኮዎችም ራስን አዘጋጅቶ መገኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
​የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አወል እንድሪስ የጸጥታ ኀይሉ በክልሉ እና በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖችን በመመከት የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
አቶ አወል “አሁን ያለንበት ወቅት የሚጠይቀው ንቁ፣ ብቁ፣ ቁርጠኛ እና ከሕዝብ ጋር በቅንጅት የሚሠራ ኀይል ነው፤ እናንተ ደግሞ የዚህ ተምሳሌት ናችሁ” ብለዋል።
ተመራቂ ሠልጣኞች በበኩላቸው ያገኙት ሥልጠና ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመግለጽ የተጣለባቸውን አደራ በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:-ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ መሪዎች እና ሠራተኞች የችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አከናወኑ።
Next articleምሥራቅ ዕዝ ዞብል ክፍለ ጦር በሰከላ ወረዳ ያሠለጠናቸውን የሰላም አሥከባሪዎች አስመረቀ።