
የቢሮው መሪዎች እና ሠራተኞች በባሕር ዳር ከተማ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልእክት የችግኝ ተከላ እንዲሁም “ደም በመለገስ ሕይወትን እንታደግ!” በሚል መሪ መልዕክት የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ አካሂደዋል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በባሕር ዳር የግብርና እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች መዳረሻ የገበያ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከናውኗል። የተተከሉት ችግኞችም ለምግብነት የሚያገለግሉ መኾናቸው ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢን ሥነ-ምኅዳር ከመጠበቅ ባለፈ የአፈር እና የውኃ ሀብትን ለማልማት፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ኀላፊው አክለውም የኑሮ ውድነትን የመከላከል ዋና ተግባር እንደተጠበቀ ኾኖ ከትልልቅ ሥራዎች ጎን ለጎን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው የለውጥ ጎዳና ውጤቱ ያማረ እንዲኾን በየቀኑ አዳዲስ ተግባራትን በብቃት መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዶክተር ኢብራሂም ፤ የሌላውን ችግር እንደ ራሳቸው በመቁጠር በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶቹ ላይ ንቁ ተሳትፎ ላደረጉ መሪዎች እና ሠራተኞች ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የባሕር ዳር የግብርና እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች መዳረሻ የገበያ ኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር ተዋቸው ወርቁ በበኩላቸው ቢሮው ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ እና የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በማዕከሉ በመደረጉ ምሥጋና አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ቢሮው በደም እጥረት ምክንያት ሊከሰት የሚችልን የሞት አደጋ ለመታደግ እና ታካሚዎች ፈጣን የጤና ማገገም እንዲያገኙ ለማስቻል ያለውን ማኅበራዊ ኀላፊነት ለመወጣት የደም ልገሳ መርሐግብር አካሂዷል።
በባሕር ዳር የደም ባንክ አገልግሎት ባለሙያ ሲስተር ዓለምዘውድ አድማሱ “ደም መለገስ ሰብዓዊነት ነው” ሲሉ ገልጸው ተግባሩ የሌሎችን ሕይወት ከመታደግ ባሻገር ለለጋሹ አዲስ የደም ሕዋስ እንዲመረት፣ የደም መቅኔ እንዲታደስ፣ የብረት መጠን እንዲመጣጠን እና ለልብ እና ደም ሥር ጤንነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።
በችግኝ ተከላ እና በደም ልገሳ መርሐ ግብሮቹ ላይ የቢሮው ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ እና የቢሮው አማካሪ አስናቁ ደረስ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች መሪዎች እና ሠራተኞች የተገኙ ሲኾን ተሳታፊዎቹ የተተከሉ ችግኞችን ቀጣይነት ባለው መንገድ መንከባከብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
