የዘመናዊው ዓለም የቴክኖሎጂ፣ የታዳሽ ኀይል እና የኢንዱስትሪ መሠረት የኾነው የማዕድን ዘርፍ በአማራ ክልል አዲስ የልማት እና የዕድገት ተስፋ ይዞ ብቅ ብሏል። የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ አድርጓል።
የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ ክልሉ በወርቅ፣ በሊቲየም፣ በፖታሽ፣ በድንጋይ ከሰል እና በሌሎች ማዕድን የተቸረውን ተፈጥሯዊ ሀብት በአግባቡ በማልማት የኢኮኖሚ ባርነትን የሚሰብሩ በርካታ ዓበይት ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ ተናግረዋል።
እንደቢሮ ኀላፊው ገለጻ የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች፦

የውጭ ምንዛሬ እና የወርቅ ምርት፦ ባለፈው የበጀት ዓመት የተገኘው 12 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በዚህ ዓመት ወደ 64 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አድጓል። 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ኾኗል። በኦፓልም የተገኘው ሀብት በተመሳሳይ ዕድገት አሳይቷል።

በሀገር ውስጥ ምርት መተካት፦ የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 131 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማዳን ተችሏል። ለክልሉ መንግሥትም 324 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግ ተችሏል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ፦
ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ለ55 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

የዕይታ እና የአስተሳሰብ ችግር ላይ ለውጥ መጥቷል

የመወቅር ለውጥ መምጣትም ተችሏል

የማዕድን ጥናት እና ምርምርን ማስፋት ስለመቻሉም አንስተዋል።

የቴክኖልጅ ዕድገት እና እውቀት ሽግግር ላይም ለውጥ ተፈጥሯል።

በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች፦ በዘርፉ በቂ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የአስተሳሰብ እና የኢንቨስትመንት እንቅፋቶች፣ የጸጥታ እና የሕገ-ወጥነት ፈተናዎች እንደነበሩም አንስተዋል።

እንደ ኀላፊው ገለጻ በ2019 በጀት ዓመት ከታቀዱ ሥራዎች መካከል፦

1ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ

የማዕድን ሀብትን ለማበልጸግ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማከናወን

የወረዳ መዋቅሮችን ተዳራሽነት ማስፋት

የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት መሥራት

የማዕድን ጥናትና ምርምርን ማስፋት እንደሚገኙበት በአብነት አንስተዋል። የመድረኩ ተሳታፊ እና የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ታየች ዘለቀ እንደ ዞን በ2018 በጀት ዓመት የማዕድን ዓይነቶችን በጥናት መለየት፣ የማዕድን ሀብት ያለበት አካባቢ መሠረተ ልማት ላይ መሥራት፣ በማዕድን ዘርፉ አማካኝነት የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ የወርቅ ምርትን ከታቀደው በላይ በማሳደግ፣ የውጭ ተኪ ምርቶችን በመተካት እና የወጭ ንግድን በማሳደግ የሀገር እና የክልሉን ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንደታቀደም ገልጸዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ እና የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን መምሪያ ኀላፊ አሕመድ አበባው ደግሞ በ2018 በጀት ዓመት እንደ ዞን የማዕድን ጥናትና ካርታ ሥራ መሥራት፣ የማዕድን ፈቃድ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ተኪ ምርት ማምረት እና የውጭ ምንዛሬ የማስቀረት አበይት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ በዞኑ ያለውን የማዕድን ሀብት በሰፊው በማስተዋወቅ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሳተፉ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
ከአነስተኛ ሥራዎች ወደ ስፋት ያለው ኢንዱስትሪያላይዜሽን መሸጋገር ዋና ትኩረት ተደርጎ ይሠራልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ