“የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የሕዝብ መረጃ የሚመነጭበት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

5
የአማራ ክልል ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የቴክኖሎጂ ቀጥታ ምዝገባ ሲስተም ማስተዋወቅ እና የ2018 በጀት ዓመት የዞኖች እና የከተማ አሥተዳደሮች የዕውቅና መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል የአማራ ክልል ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ የምዝገባ አገልሎቱን ከወረቀት ወደ ቀጥታ ምዝገባ ማሸጋገራቸውን ገልጸዋል። ከወረቀት ወደ ቴክኖሎጂ የተደረገው ሽግግር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሃብት ብክነትን ለመከላከል፣ ሀሰተኛ ሰነድን ለመከላከል፣ ጊዜ እና ጉልበትን ለመቆጠብ ያስችላል ነው ያሉት።
ሁሉንም የምዝገባ ጣቢያዎች ወደ ቴክኖሎጂ ለማሻገር የሌሎች እገዛ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ከወረቀት ወደ ቴክኖሎጂ የተደረገው ጉዞ ስኬታማ እንደኾነ አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እውን እንዲኾን በትብብር መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። እየተደረገ ያለው ምዝገባ ለሕግ፣ ለስታትስቲክስ እና ሌሎች ሥራዎች እንደመረጃ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ለመንግሥት አሥተዳደር ውጤታማነት አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የሕዝብ መረጃ የሚመነጭበት ነው ብለዋል። የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ መረጃ የመንግሥት እና የሕዝብ አሥተዳደር ግንኙነትን የሚያሳልጥ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅዶች እንዲታቀዱ፣እንዲጎለብቱ እና ውጤታማ እንዲኾኑ የሚያደርግ ሥርዓት ነው ብለዋል።
ተደራሽ እና ጥራት ያለው መረጃ ማመንጨት ደግሞ በብዙ እንደሚጠቅም ገልጸዋል። ለዘመናዊ እና ጥራት ላለው መረጃ ትኩረት እንደተሰጠውም አንስተዋል።
የመረጃ ተደራሽነት እና ጥራት ችግርን ለመቅረፍ ቴክኖሎጂ ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ከተጀመረ የቆዬ ታሪክ ቢኖረውም በተደራሽነቱ እና በጥራቱ ፈተና ውስጥ ቆይቶ የኖረ ነው ብለዋል። ለዓመታት በፈተና ውስጥ የቆዬውን ሥራ የሚያሻሽለው በቴክኖሎጂ መደገፍ መኾኑን ገልጸዋል።
ሥራውን በቴክኖሎጂ የደገፉ ሀገራት የመንግሥት አሥተዳደርን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ማድረግ መቻላቸውን አንስተዋል። ሥራውን በቴክኖሎጂ መደገፍ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የመረጃ ጥራትን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት።
በወረቀት የሚደረግ ምዝገባ ( የሰው ንክኪ) ተደራሽነትን ከማዛባቱም በላይ የመረጃ ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው ብለዋል። ሥራውን በቴክኖሎጂ መደገፍ ግልጽ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መረጃን ለመያዝ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት በርካታ ባለድርሻ አካላት ተዋናይ የሚኾኑበት መኾኑን ገልጸዋል። የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት በሚሰጠው ውጤት የማይጠቀም ተቋም እና የኅብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ተናግረዋል። ይህ ዘርፍ የማኅበረሰብ ምህንድስና ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።
መረጃን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ከወረቀት ወደ ቴክኖሎጂ በመሸጋገሩ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ ወጭን ይቆጥባል ብሎም የመረጃ ደኅንነትን ይጠብቃል ነው ያሉት። ተቋሙ እዚህ እንዲደርስ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
✍️ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሰላም እና ኅብረት ሥራ፦ ሁለቱ የልማት ገጾች !
Next articleአማራ ክልል 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርቧል።