ሰላም እና ኅብረት ሥራ፦ ሁለቱ የልማት ገጾች !

4
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክን አካሂዷል።
በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ እንዲሁም የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒዬኖች ለሀገር ኢኮኖሚ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ዘርፉ የኢንዱስትሪ አብዮትን በማሳደግ በሁሉ አቀፍ እምርታ ውስጥ የሚገባ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ የሚፈጥር እንደኾነ ነው የገለጹት። ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እንደኾነም አንስተዋል። በተለይም ዘመናዊ ግብርናን ለመገንባት ከፍተኛ አቅም የሚኾኑ ናቸው ብለዋል።
ይሁንና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ዘሪሁን የክልሉ ቁልፍ አቅጣጫ ሰላምን ማጽናት በመኾኑ ለሰላም መረጋገጥ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ለዩኒዬኖች እና ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ውጤታማነት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ ኮሚሽኑ በ2018 በጀት ዓመት በሪፎርም እና በሌሎችም ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ገበያውን በማረጋጋት የግብይት ሥርዓቱን የተሻለ ማድረግ እና በዘርፉ ሕገ ወጥነትን ለመከላከልም ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል ነው ያሉት።
የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተከናወነው ተግባር በባሕር ዳር ከተማ ብቻ ከ9ዐዐ በላይ ማኅበራት ተደራጅተው ዜጎች የመኖሪያ ቤት ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሐም ወርቁ በከተማው የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ማኅበራትን የማደራጀት እና ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። አሠራሩን ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተለይም የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት ተችሏል ነው ያሉት።
የአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን ዋና ሥራ አሥኪያጅ መሠረት ወርቄ ዩኒዬኑ ግብዓት በወቅቱ ወደ አርሶ አደሮች መንደር እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ ዘመናዊ ግብርና እንዲገነባ ትራክተር ገዝቶ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው ዩኒዬኖች፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ፈጻሚ አካላት እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሰው ሰራሽ አስተውሎት ለታዳጊ ሀገራት ምን ዕድል አመጣ?
Next article“የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የሕዝብ መረጃ የሚመነጭበት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ