ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ800 ሚሊዮን ብር የቆዳ እና የጫማ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ስምምነት ተፈራረመ።

16
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስምምነቱን የተፈራረመው ከጣሊያን ማርኬ ሪጅን ዓለም አቀፍ ትብብር እና ከሲ ቪ ኤም ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ጋር ነው።ፕሮጀክቱ በቆዳ ፕሮሰሲንግ፣ በጫማ ዲዛይን እና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ያለመ ነው።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ያለውን ተሞክሮ ለማሳደግ ስምምነቱ ይጠቅመዋል።
ይህ ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ትልቅ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለልምድ ልውውጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኢትዮጵያን የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት እና ጥራት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ከዘርፉ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንደምትኾን ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ፋይናንስ ከጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የተገኘ ሲኾን ለሁለት ዓመታት የሚቆይ እና በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚተገበር መኾኑንም አንስተዋል። ለፕሮጀክቱም ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስረድተዋል።
የጣሊያን ማርኬ ሪጅን ዓለም አቀፍ ትብብር አስተባባሪ ናታሊኖ ባርቢዚ በበኩላቸው ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል በቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ያለውን ትብብር የሚያጠናክር መኾኑን ገልጸዋል።
በገበያ ትስስር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተማሪዎች ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአካዳሚክ ትብብር እና በልምድ ልውውጥ አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ስምምነቱ የአፍሪካ የቆዳ ዘርፍ ትብብርን በአዲስ እንደሚያስጀምርም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የትብብር ስምምነቱን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) እና የጣሊያን ማርኬ ሪጅን ዓለም አቀፍ ትብብር አስተባባሪ ናታሊኖ ባርቢዚ ተፈራርመዋል።
✍️ዘጋቢ:-አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበዳንግላ ወረዳ ለተገነቡ መሠረተ ልማቶች የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የጸጥታ ኀይል ሚና ከፍተኛ ነው።
Next articleበደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የተመረቁ የጸጥታ ኀይሎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተዘጋጅተዋል።