
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ተቋሙ በዓመቱ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።
“ከትላንት ተምረን ነገን ልናሳምር የምንችለው ዛሬን በሚገባ ስንጠቀም ነው” ያሉት ዋና ሥራ አሥፈፃሚው ትላንትናን የምንነጋገረው ነገን ውጤታማ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ከባለፈው ዓመት ከተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ጠንካራ ጎኖች እና ውስንነቶች በመማር የ2019 በጀት ዓመትን በጋራ በመሥራት ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
መድረኩ በመመካከር ያለፈውን የመቋጨት እና የቀጣዩን በጀት ዓመት ውጤታማ ማድረግ ላይ ስንቅ የሚያዝበት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
አሚኮን ይበልጥ ውጤታማ እና ስኬታማ ለማድረግ ካለፉት ዓመታት ጥንካሬዎች እና ድክመቶች በመማር ለቀጣዩ በጀት ዓመት የተሻለ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
እያንዳንዱ ባለሙያ በጋራ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት “ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት በማሰብ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
አሚኮን የበለጠ ለማሻሻል ጥራትን በቁርጠኝነት መተግበር፣ ሁልጊዜም አዲስ ነገር ማሰብ፣ ለለውጥ ዝግጁ መኾን እና አዳዲስ እሳቤዎችን መጨመር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ተቋሙ በፈተና ውስጥ ኾኖ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲፀና፣ ሀገራዊ አንድነት እንዲገነባ፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎች፣ በጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እና በሌሎችም የተቋም ግንባታ ሥራዎች ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑንም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
