ከ40 ችግኝ እስከ ተስፋን መትከል፤ የትውልድ፣ የምጣኔ ሀብትና የዓለም አቀፍ አብነት ጉዞ።

15
🌱
በ2011 ዓ.ም “በአንድ ሰው 40 ችግኝ” በሚል ታላቅ ሀገራዊ መነቃቃት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት ተከታታይነት ባለው እና እያደገ በመጣ ሀገራዊ ራዕይ ሲመራ ቆይቷል። ይህ ጉዞ “እየተጠነቀቅን እንተክላለን” ከሚለው የእንክብካቤ እና የጥንቃቄ መርህ ተነስቶ “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል ሰፊ የሽፋን ራዕይ 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
ላለፉት ዓመታት የተተከሉት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የሀገሪቱን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የተራቆቱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ረገድ የነበራቸው ሽፋን እጅግ የላቀ ነው። ይህ ተግባር “ዐሻራችን ለትውልዳችን” በሚለው መሪ መልዕክት እንደተገለጸው የአሁኑ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ ሊያወርሰው የሚችለው ሕያው እና የማይጠፋ አረንጓዴ ሀብት ኾኖ ተመዝግቧል።
አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያውያንን በጋራ ዓላማ ስር ያሰለፈ ትልቅ የማስተሳሰሪያ ገመድ ኾኖም ይነሳል። “የምትተክል ሀገር የሚፀና ትውልድ” የሚለው የ2016 ዓ.ም መሪ መልዕክት በግልጽ እንደሚያሳየው መርሐ ግብሩ የዜጎችን የተፈጥሮ ጥበቃ ባሕል በእጅጉ አሳድጓል፤ ወጣቶች፣ አዛውንቶች እና ሕጻናት ሳይቀሩ በየዓመቱ ክረምት ሲገባ በጉጉት የሚጠብቁት ሀገራዊ ባሕልን ፈጥሯል። ይህ የጋራ ስሜት ማኅበራዊ አንድነትን ከማጠናከሩም ባሻገር ኅብረተሰቡ ለአካባቢው ያለውን የባለቤትነት ስሜት በማሳደግ፣ ችግኞችን ከመትከል አልፎ በመንከባከብ እና በማሳደግ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርጓል።
“ነገን ዛሬ እንትከል” በሚለው መንፈስም ማኅበረሰቡ የዛሬው ጥረቱ የነገን የኑሮ ዋስትና እንደሚያረጋግጥለት ተገንዝቦ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
አረንጓዴ ዐሻራ ባለፉት ዓመታት ትልቅ መዋቅራዊ ሽግግር አድርጓል። መጀመሪያ አካባቢ ትኩረቱ የደን ሽፋንን ማሳደግ ላይ የነበረ ቢኾንም በሂደት ወደ አግሮ-ፎረስትሪ ወይም ለምግብነት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ወደሚውሉ ችግኞች አድጓል።
እንደ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ቡና እና ፖም ያሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት ማዘጋጀት እና መትከል መጀመሩ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እያሳደገ መምጣቱን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ከችግኝ ማፍላት እስከ እንክብካቤ ባለው ሂደት በመላው ሀገሪቱ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ መኾኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
የደን ሽፋኑ ወደ 23 በመቶ አድጓል። የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን አሳድጓል። ይህም በተረጂነት ሰበብ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሚፈልጉ ኅይሎችን ሴራ ያከሸፈ የዘመኑ ትልቁ የልማት አውታር ነው።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ የኀይል ማመንጫዎችን ከደለል በመታደግ የኢኮኖሚ ዕድሜያቸውን የሚያራዝም ታላቅ ኢንቨስትመንትም ነው።
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ አድርጓታል። የዓለም ሙቀት መጨመር እና የአየር ንብረት መዛባት የዓለማችን ትልቁ ስጋት በኾነበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ 56 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ለሌሎች ሀገራት በተለይም ለአፍሪካውያን ትልቅ አብነት ኾናለች።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚለው መሪ መልዕክትም ዓለም በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቀውሶች በሚፈተንበት በአሁኑ ወቅት ተፈጥሮን በማከም ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማስቻል እንደሚቻል አሳይታለች።
የ2018 ዓ.ም መሪ መልዕክት የኾነው “ተስፋን እንትከል” የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ ዛፍ የመትከል ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የሀገርን የረጅም ጊዜ ራዕይ፣ የትውልድን ብሩህ ተስፋ፣ የኢኮኖሚን መሻሻል እና የተፈጥሮን ሚዛን የመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ፀጋ መኾኑን የሚያስመሰክር ነው።
✍️ዘጋቢ:-ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዓባይ ባንክ ደንበኞቹ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያስችል ካርድ ይፋ አደረገ።
Next article✨ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮች እፎይታ!