
ዓባይ ባንክ ይፋ ያደረገው ክላሲክ ቪዛ ካርድ ደንበኞች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የኤ ቲ ኤም እና ፖስ ማሽኖች ላይ ገንዘብ ማስተላለፍ እና ክፍያዎችን መፈጸም እንዲችሉ ያደርጋቸዋል።
ባንኩ ባሉት ኤ ቲ ኤም ማሽኖች በተጠናከረ የኢንተርኔት እና የሞባይል ባንኪንግ አማራጮች ሰፊ የዲጂታል አገልግሎቶችን ይሰጣል።
አሁን ደግሞ ተደራሽነቱን እና ዘመናዊነቱን በማስፋት ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያ መሪ ከኾነው ቪዛ ጋር በመተባበር ደንበኞች ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሳይጠበቅባቸው ደኅንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያስችል ዓባይ ክላሲክ ኢንተርናሽናል ፕሪፔይድ ቪዛ ካርድን አስተዋውቋል።
የዓባይ ባንክ ሥራ አሥፈጻሚ የኋላ ገሰሰ ካርዱ የኦንላይን የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግብይቶችን ለመፈፀም አመች የኾነ እና ባንኩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ለማሳደግ እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማቃለል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መኾኑን ጠቁመዋል።
ካርዱ ከዓለም አቀፍ እቃ አቅራቢዎች ጋር ግብይት ከሚያደርጉ የንግድ ባለቤቶች ጀምሮ ዓለም አቀፍ የዲጂታል አማራጮችን እስከሚጠቀሙ ወጣቶች እና ድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎችን እስከሚፈጽሙ ተጓዦች ድረስ ያሉትን የልዩ ልዩ ክፍሎች ፍላጎት ለማሟላት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
የቪዛ ኢትዮጵያ ካንትሪ ማናጀር እና የምሥራቅ አፍሪካ ክላስተር ኀላፊ ያሬድ እንዳለ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ አንቀሳቃሽ መኾኑን አንስተዋል።
ከዓባይ ባንክ ጋር የተደረገው አጋርነት ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎቶች ያለውን ተደራሽነት እንደሚያሰፋ እና ግለሰቦች በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የዓባይ ክላሲክ ቪዛ ካርድ መጀመር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ለማጠናከር ሌላው ትልቅ ምዕራፍ ሲኾን ለደንበኞችም በዓለም ዙሪያ ግብይቶችን ለማከናወን ቀላል፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ መንገድን ይፈጥራል ተብሏል።
#AMECO #AbayBank #VisaCard #DigitalBanking #Ethiopia
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
