
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጉጉት የሚጠበቅ ማኅበራዊ እሴት እየኾነ መምጣቱን የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል።
በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በተካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ ታዳጊዎችም ተሳትፈዋል።
በደባርቅ ከተማ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አሻራውን ሲያሳርፍ ያገኘነው ታዳጊ ኤልያስ በለጠ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው።
“ዛሬ የምንተክላት ችግኝ ነገ አድጋ ትልቅ ዛፍ ትኾናለች፤ ለእኛም የማጥኛ ጥላ እና መጠለያ የምትኾን ናት በማለት ሀሳቡን አጋርቶናል።
ሌላኛዋ ታዳጊ መሰሉ እያያው የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በራሷ ተነሳሽነት በመሳተፍ የተከላ ሥራ ማካሄዷን ገልጻለች።
ታዳጊዎቹ መርሐ ግብሩ የተከናወነበት ቦታ በሚማሩበት ትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚገኝ በመኾኑ ትምህርታቸውን ከመከታተል ጎን ለጎን በቅርበት በመገኘት በቀጣይ የእንክብካቤ ተግባራትን እንደሚያከናውኑም አንስተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፋሲካ መረሳ የሕጻናቱ ተሳትፎ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በትውልድ መካከል የሚሸጋገር ታሪካዊ ሁነት እየኾነ መምጣቱን እንደሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ ከ80 በመቶ በላይ ከፍ ለማድረግ እንደሚሠራ አብራርተዋል።
#AMECO #greenlegacy #Ethiopia
#ደባርቅ #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ደረጀ ደርበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
