
በ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተናን ከወሰዱ 1ሺህ 581 የደብረ ታቦር ከተማ መደበኛ ተማሪዎች መካከል 43 በመቶ የሚኾኑት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ገልጿል።
በፈተናው ድንቅ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል የዳልሻ ትምህርት ቤት ተማሪ ተመስገን ሉሌ (579) እና ተማሪ ትህትና ክንዱ (532) እንዲሁም የደብረ ታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዳኘው አበበ (558) ይገኙበታል።
ተማሪዎቹ ለስኬታቸው ቁልፉ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ በርትቶ ማንበብ፣ የቡድን ውይይት፣ የትዕግስት እና ቁርጠኝነት ውጤት እንዲሁም የወላጆች እና መምህራን ያልተለየ ድጋፍ መኾኑን ተናግረዋል።
የቀጣይ ዓመት ተፈታኞችም የባለፉት ዓመታት ፈተናዎችን በመከለስ ለከፍተኛ ውጤት እንዲዘጋጁም መክረዋል።
የተማሪ ዳኘው አበበ ወላጅ ሻምበል አበበ ሹመት እና የሂሳብ መምህሩ መኮንን መስፍን እንደገለጹት ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ በተሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶች፣ መምህራን የማስተማሪያ ይዘቶችን ቀድመው በማጠናቀቃቸው እና በወላጆች በተፈጠረ ምቹ ሁኔታ ውጤቱ የተሻለ መኾኑን ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ በበኩላቸው የተሠሩ ሰፊ ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው የትምህርት ጥራትን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት እንዲሠሩ እና የተማሪዎችን ዲሲፕሊን እና የንባብ ልምድ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
