
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የ2019 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አሊ ተፈራ እንደገለጹት በትምህርት ዘመኑ ከ198 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ የታቀደ ሲኾን እስካሁን ባለው አፈፃፀም 150 ሺህ ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል።
በቀሪ የምዝገባ ቀናት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል። በተጨማሪም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ከ15 ሺህ በላይ ደርዘን ደብተር መሠብሠቡን ኀላፊው ገልጸዋል።
የከሚሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አረቡ አሊ በበኩላቸው ከተማ አሥተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው ባለፈው ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና የታዩ ክፍተቶችን በማረም የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ከፍ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
የከሚሴ ከተማ ቁጥር አንድ ጠቅላላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መሀመድ እሸቱ በትምህርት ቤቱ ከአምናው በተሻለ የተማሪዎች የማለፍ ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰው በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መምህራን የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ ሲመዘገቡ አሚኮ ያነጋገራቸው ተማሪዎች በበኩላቸው በክረምቱ አጋዥ መጽሐፍትን በማንበብ ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና በአዲሱ የትምህርት ዘመንም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
