በክልሉ ከ108 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊገነቡ ነው።

25
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2019 ዕቅድ ትውውቅ እና በአዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) በ2018 በጀት ዓመት በሪጅዮፖሊታንት እና በሌሎች ከተሞች ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። ከመደበኛ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አኳያ 95 በመቶ የሚኾኑት
መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል። የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ሥራም በ230 ከተሞች ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል። 606 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ደግሞ በከተማ ምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
📌 እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ የ2019 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች፦
🏘የቤት ልማት፦ በ18 ከተሞች በተዘጋጀ 150 ሄክታር መሬት ላይ በመንግሥት፣ በግል፣ በሪል እስቴት እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት ከ108 ሺህ በላይ ቤቶችን በፍጥነት ገንብቶ የማኅበረሰቡን የቤት ችግር መፍታት እና ኑሮውን ማሻሻል።
🖥ዲጂታላይዜሽን፦ አገልግሎቶችን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለማድረግ በበርካታ ከተሞች በበይነመረብ (ኦንላይን) እና በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መሰጠት ይጀምራል።
🛣ስማርት ሲቲ፦ በ19 ከተሞች ስማርት ሲቲ ይተገበራል። የቴሌ፣ ውኃ፣ መብራት እና መንገድ ተቋማት የተቀናጀ አሠራር መፍጠርን በአብነት አንስተዋል።
👉አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ ላፉት 18 እና 19 ዓመታት ሢሠራበት የነበረውን አሠራር በመቀየር ከተሞች የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ምርቶች አምራች፣ የቴክኖሎጂ አፍላቂ እና የንግድ ማዕከል እንዲኾኑ የሚያስችል እና የገጠር-ከተማ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክር እንደኾነም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
በድረኩ የተሳተፉ የከተሞች የሥራ ኀላፊዎችም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኮሪደር እና የቤቶች ልማት፣ የተቋማት ግንባታ እና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማት ተግባራትን በዋናነት ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን አንስተዋል።
በቀጣዩ በጀት ዓመትም የተጀመሩ ልማቶችን ማስቀጠል፣ የቤቶች ልማት፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በትኩት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
✍️ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleወጭ እና ገቢን በማጣጣም የተረጋጋ የፋይናንስ አሥተዳደር መፍጠር ተችሏል።
Next articleየከሚሴ ተማሪዎች በክረምቱ አጋዥ መጽሐፍትን በማንበብ ዝግጅት አድርገዋል።