
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ግብ መሠረት በማድረግ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን እንደገለጹት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነበር።
በበጀት ዓመቱ በመንግሥት በጀት እና በአጋር ድርጅቶች በኩል የፋይናንስ አቅርቦቱን በማሳደግ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተደረጉ የትብብር ስምምነቶች 18 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ለክልሉ መንግሥት ገቢ የተደረገ ሲኾን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ላቅ ያለ አፈጻጸም መኾኑን አቶ አታላይ ጠቁመዋል።
የልማት የፋይናንስ አቅርቦት በመንግሥት በጀት ብቻ የሚሳካ ባለመኾኑ በበጀት ዓመቱ 25 ቢሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ መሠብሠብ ተችሏል።
የክልሉን የፋይናንስ መረጃ በዲጂታል ሥርዓት በማደራጀት ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የሂሳብ አሠራር ተዘርግቷል። ከዚህ ቀደም የዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚ ያልነበረውን የገጠር ማኅበረሰብ አካታች በማድረግ የብድር አቅርቦት እንዲሳለጥ እና ኅብረተሰቡ ያለማስያዣ የብድር ተጠቃሚ እንዲኾን ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ የበጀት አሥተዳደር፣ የፋይናንስ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ዘመኑን የዋጀ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት እንዲኖር ታስቦ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አሥተዳደር አዋጅ እና መመሪያዎች ተሻሽለው ተዘጋጅተዋል።
ቢሮው በ2019 በጀት ዓመት የክልሉን የውስጥ ገቢ አቅም ለማሳደግ እና የገቢ አሠባሠብ ሥርዓቱን ለማጠናከር፣ የመንግሥት ገንዘብ እና ንብረት አጠቃቀምን በጥብቅ ለመከታተል የሕዝብ ሀብት ለታለመለት የልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ እንዲውል ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
