
የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ በመክፈቻ ንግግራቸው ፕሮጀክቶች በአካባቢ እና በማኅበረሰብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያደርሱ መቆጣጠር አንደኛው የተቋሙ ተግባር እና ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረትም በ2018 በጀት ዓመት፦
በደን ሀብት ጥበቃ እና ልማት ባለፉት ሁለት እና ሦሥት ዓመታት በተከናወነው ሥራ የክልሉ የደን ሽፋን ማደጉን የገለጹት ምክትል ኀላፊው በበጀት ዓመቱ ከከሰል፣ ዕጣን፣ ሙጫ እና ሌሎች የደን ውጤቶች ዝውውር ከ249 ሚሊዮን ብር በላይ ተሠብሥቦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የበጀት እጥረት እና የጸጥታ ችግርን ተከትሎ የተቋሙ ንብረቶች መውደማቸው ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደነበሩ አውስተዋል።
ባለሥልጣኑ በ2019 በጀት ዓመት የደን ውጤቶች ዝውውርን በአግባቡ ማሥተዳደር፤ ለተፈጥሮ ደኖች ልዩ ጥበቃ ማድረግ፤ የጥብቅ ደኖችን ቁጥር ማሳደግ እና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ክትትል እና ቁጥጥርን ማጠናከር የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የዞን ተጠሪ ተቋማት መሪዎች በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት የአካባቢውን ጸጋ በመለየት፤ ማኅበራትን በማደራጀት እና ባለሀብቶችን በመሳብ ከደን ውጤቶች ገቢ የመሠብሠብ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። በዘርፉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ከአምራቾች፣ ከባለሀብቶች እና የዕጣን፣ ከሰል፣ ከርቤ እንዲሁም ሙጫ ሀብቶች ካሉባቸው አካባቢ ወጣቶች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
