“በፈተና ውስጥ ያለፈ ስኬት ተመዝግቧል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

11
በአማራ ክልል በ2018 በጀት ዓመት የማኅበራዊ ዘርፍ ተቋማት ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የማኅበራዊ ዘርፍ ተቋማት በክልሉ የሕዝቡን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥ በፈተናዎች ታጅበውም ቢኾን ውጤታማ ተግባራትን መሥራታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የአገልግሎት አሠጣጥ ተደራሽነት እና ጥራትን የማሳደግ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት። የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ተሠርተዋል ብለዋል።
በቀጣይ በ2019 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬታማ ተሞክሮዎችን በማስፋት፤ ክፍተቶችን በድጋፍ እና ክትትል ማረም ይገባል ብለዋል። በቅንጅት በመሥራትም የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት እና የሕዝቡን ፍላጎት ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በእናቶች፣ በሕጻናት፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልኾኑ በሽታዎች መከላከል ሥራዎች ላይ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል 465 ጤና ጣቢያዎች የአልትራሳውንድ አገልግሎት እየሠጡ ነው። በተቋማት ዲጂታላይዜሽን ሥራም 23 ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ወረቀት አልባ የሕክምና ሥርዓት እየተገበሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እጥረትን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት። ፍትሐዊ፣ ጥራት ያለው፣ ተደራሽ እና ዘላቂ የኾነ የጤና አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ ለመስጠት እና ዘላቂ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት መሠራቱንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በ2018 በጀት ዓመት የትውልድ ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን የታቀዱ ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች፤ የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ፤ የተማሪዎች ምዝገባ እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ እንደኾነም አንስተዋል። እስካሁን ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውም ጠቁመዋል። ሁሉንም ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ሁሉም በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 149 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
Next articleተፈጥሮን በመጠበቅ የገቢ ምንጭ ማድረግ ተችሏል።