
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እያካሄደ ነው።
ባለፈው በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን 96 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ አስቀምጦ ሲሠራ መቆየቱን የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) አስታውቀዋል። በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 100 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 149 ሺህ የሚኾኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራውን ታማኝ እና ከሐሰት ሪፖርት የጸዳ ለማድረግ አሠራሮችን የማዘመን (ዲጂታላይዜሽን) ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ከተፈጠረው አጠቃላይ የሥራ ዕድል ውስጥ 76 በመቶው በሲስተም የተመዘገቡ ናቸው፤ ቀሪዎቹ 24 በመቶዎቹ የኢንተርኔት አገልግሎት በሌለባቸው አካባቢዎች በወረቀት የተመዘገቡ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን ይበልጥ በማዘመን በዘንድሮው በጀት ዓመት በክልል ደረጃ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎችን በ65 ሺህ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ መቀመጡንም አንስተዋል።
በተለይም የመረጃ ሥርዓቱን ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አንድ ዜጋ በአንድ ማዕከል ብቻ ተመዝግቦ ዕውነተኛ መረጃ እንዲያዝ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ከቴሌግራም ጋር በማገናኘት ለተጠቃሚዎች የሥራ ዕድሉ መፈጠሩን የሚያረጋግጥ መልዕክት በቀጥታ ወደ ስልካቸው እንዲላክ ይደረጋል ብለዋል።
ወደ ሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች የክህሎት ሥልጠና ትኩረት እንደተሰጠውም አስታውቀዋል። ማንኛውም ዜጋ በክልሉ በሚገኙ 246 ኮሌጆች በቂ የክህሎት፣ የዕውቀት እና የአስተሳሰብ ሥልጠና ወስዶ እና ብቁ ኾኖ ወደ ሥራ እንዲሰማራ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሥራውም በየዞኑ ያሉ ጸጋዎችን መሠረት በማድረግ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት እና በግብርና ዘርፎች ተከፋፍሎ የሚከናወን ይኾናል ነው ያሉት።
ሥልጠናውን እና አደረጃጀቱን ተከትሎ የመስሪያ ቦታ አቅርቦትን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ኮንቴነሮች እና ሼዶችን በማስመለስ ለአዳዲስ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ቁርጠኛ አቋም መያዙንም አስታውቀዋል።
በቀጣይም ከዚህ ቀደም የነበሩትን ኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍተቶችን ለመፍታት ከአሠልጣኞች፣ ከኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የተደራጁ ማኅበራትን በቅርብ በመከታተል በስታንዳርዱ መሠረት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
