የመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቁ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።

7
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ በወንጀል እና በፍትሐብሔር ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል። ተቋማዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የባለሙያ እና የመሪ ቅንጅትን መሠረት ተደርጎ ስለመሠራቱም ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ 15 አዋጆች፣ 65 ደንቦች እና 31 መመሪያዎች በቢሮው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን እና ቀልጣፋ በማድረግ 669 ሺህ 684 ለሚኾኑ ተገልጋዮች አገልግሎት መሰጠቱንም አብራርተዋል።
394 ሺህ 678 ሰነዶችን ማረጋገጥ እና መመዝገብም ተችሏል። ከዚህም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ስለመቻሉ ገልጸዋል። ተከራክሮ የማሸነፍ ምጣኔን በማሳደግ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗልም ነው ያሉት።
የመዛግብት ውሳኔ አሰጣጥ ቅልጥፍናን በማሳደግ በ21 ሺህ 731 መዛግብት ላይ ውሳኔ በመስጠት የማጣራት አቅምን ማሳደግ ስለመቻሉም አንስተዋል። ​በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር በኩል ወንጀል መከላከል፣ ጥፋተኛ ማስቀጣት እና ንብረት ማስመለስ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱንም አብራርተዋል።
በወንጀል ምክንያት የተመዘበረን ንብረት ማስመለስ የ2019 በጀት ዓመት ቁልፍ ጉዳይ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። “ወንጀልን የሚቀንሱ፣ የመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቁ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል” ነው ያሉት።
ቅንጅታዊ አሠራርን በማዳበር፣ የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅምን በማሳደግ፣ የአሠራር እና የሥነ-ምግባር ግድፈቶችን በመከታተል ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ፍትሐዊ የግብር ሥርዓትን ለማረጋገጥ ተሠርቷል”
Next articleበውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 149 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።