“ፍትሐዊ የግብር ሥርዓትን ለማረጋገጥ ተሠርቷል”

7
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መርሐግብር እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፍቅረ ማርያም ደጀኔ በክልሉ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በግብር አሠባሠብ ሂደት ላይ እንቅፋት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በ2018 ዓ.ም የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ስኬታማ ገቢን ለመሠብሠብ ዕድል ፈጥሯልም ነው ያሉት። የክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ወደ ሥራ መግባቱን መነሻ በማድረግ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በትኩረት በመሠራቱ ውጤታማ መኾን ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 100 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 93 ቢሊዮን ብር እንደተሰበሰበ ገልጸዋል። የዕቅዱን 92 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካት ተችሏልም ብለዋል።
ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ54 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ገልጸዋል። የተዛባ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት የኾኑ 149 በየመንገዱ ተዘርግተው የነበሩ ኬላዎች እንዲነሱ የክልሉ መንግሥት በመሥራቱ የገቢ አቅም እንዲያድግ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በተቋሙ ነባር ባለሙያዎች ጥናት በማድረግ እና በቴክኖሎጅ የተደገፈ አገልግሎት በመሥጠት ፍትሐዊ የግብር አሠባሠብ ሂደትን ለማከናወን ተሠርቷል ነው ያሉት።
በግብር ተመን ላይ ቅሬታ የሚያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል። ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዞኖች እና ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች የዕውቅና እና ምሥጋና መርሐ ግብር እንደሚያካሂድም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየጳጉሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል ስያሜ ይከበራሉ።
Next articleየመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቁ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።