የዜጎችን እርካታ የሚያረጋግጡ አሠራሮች ወደ ተግባር ገብተዋል።

14
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቸአምላክ ገብረማርያም እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ከተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።
በተለይም የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርምን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን የማዘጋጀት እና የትግበራ ስትራቴጅ የመንደፍ ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በመጀመሪያው ዙር ስምንት ተቋማት ተለይተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማድረግ ሰፊ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች ስለመከናወናቸውም አንስተዋል። በሁለተኛ እና በሦሥተኛ ዙር ወደ ተግባር ለሚገቡት ተቋማትም አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።
የአገልግሎት አሠጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕል አገልግሎት ውጤት እያመጣ እንደኾነም ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ስድስት ማዕከላት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጋቸውን አንስተዋል።
እስከ አሁን ወደ ሥራ በተገባባቸው በስድስቱ ማዕከላትም በመሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ የኅብረተሰቡ እርካታ 99 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። የእርካታ መጠን ልኬቱ በቴክኖሎጂ የሚለካ በመኾኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማነት በትክክል የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል።
ማዕከላትን የማስፋፋት፣ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ወደ ማዕከላት የማስገባት፣ የተጀመሩትን አገልግሎቶች ጥራታቸውን የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
በቀጣይ 2019 በጀት ዓመት ከ155 በላይ በሚኾኑ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ላይ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
✍️ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየከሚሴ ተማሪዎች በክረምቱ አጋዥ መጽሐፍትን በማንበብ ዝግጅት አድርገዋል።
Next articleበደብረ ታቦር ከተማ 43 በመቶ የሚኾኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን ተቀላቅለዋል።