
በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአራት የገጠር ቀበሌዎች እና በአምስት ተፋሰሶች በሕዝባዊ ተሳትፎ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ የተገኙት የከተማው ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ይበልጣል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች ለአርሶ አደሮች እና ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
ችግኝ መትከል ያለውን ጥቅም የተረዳው የአካባቢው ነዋሪም በዚህ ዓመት እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐግብር በስፋት እየተሳተፈ ነው ብለዋል። የተተከሉ ችግኞችንም በሚገባ ተንከባክቦ ለፍሬ ለማብቃት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኀይለኢየሱስ ሰሎሞን በበኩላቸው ልማቱ የአየር ንብረት ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ሥራው ወደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚሄደውን የአፈር ደለል በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ አሚኮ ያገኛቸው ወይዘሮ አዝመራ ጌትነት እና ቄስ ሳለአምላክ አለምነው የተተከሉት የቡና፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሙዝ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚረዱ ጠቁመዋል።
የተከሉትን ችግኞች እንደ ልጅ በመንከባከብ እና ከእንስሳት በመጠበቅ ለፍሬ ለማብቃት ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
#AMECO #greenlegacy #Ethiopia🌱🇪🇹
#ደብረ_ታቦር #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
