የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማናሳካው እንደሌለ ማሳያ ነው።

11
የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እየተካሄደ ይገኛል።

ያነጋገርናቸው የከሚሴ ከተማ እና የደዋ ጨፋ ወረዳ ነዋሪዎች የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ በንቃት እየተሳተፉ መኾኑን ተናግረዋል። በዘንድሮው መርሐ ግብርም በተለይ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ማንጎ እና አቦካዶ የመሳሰሉ ችግኞችን እየተከሉ መኾኑን ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ ጀማል አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከዚህ በፊት የተተከሉ ችግኞች ሥነ ምህዳርን በማስተካከል እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የአፈር ለምነትን ከማሻሻሉ እና ምርታማነትን ከማሳደጉም ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ያለ ኢኒሼቲቭ መኾኑንም ገልጸዋል።

በአንድ ጀምበር ተከላውም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እና በ45 ተፋሰሶች ላይ እየተተከለ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ “ኢትዮጵያውያን እየመከሩ ባለበት ወቅት የአንድ ጀምበር ተከላው መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው” ገልጸዋል። አረንጓዴ አሻራ ላይ የምንሠራው ሥራ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚን ለማሳለጥ እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ምርት እንዲሰጡ ለማድረግ ሁሉም አካል ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእስከ ቀኑ 9 ሰዓት 700 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ
Next article“በክልሉ አረንጓዴ ዐሻራ የመሬት መራቆትን በመከላከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው” የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ኢብራሂም ኡስማን