
በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልእክት እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በሲዳማ ክልል ደቡባዊ ሲዳማ ዞን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአለታ ወንዶ ወረዳ ጎዋዳሞ ቀበሌ የችግኝ ተከላ ተካሂዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሮች የተራቁቱ አካባቢዎች እንደገና እንዲለመልሙና እንዲያንሰራሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በተለይም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና የገቢ አቅምን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
