
የሰሜን ጎጃም ዞን በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ወገልሳ ቀበሌ ጪጫ አካባቢ” ተስፋን እንትከል”በሚል መሪ መልዕክት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አሥተዳዳሪ ተመሥገን ደግአረገ “ችግኝ መትከል የሥራዎች ሁሉ እናት፥ የሥራዎች ሁሉ አውራ ነው” በሚል እሳቤ የአንድ ቀን ጀንበር ችግኝ ተከላ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በወረዳው በአንድ ጀንበር መርሐ ግብር በ44 አካባቢዎች እና በ522 ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ እየተተከለ መኾኑን ተናግረዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በተጀመረው የአንድ ቀን ጀምበር ችግኝ ተከላ በዞኑ 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ እንደሚተከል ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ ቡና እና አቮካዶን ጨምሮ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
በአንድ ቀን ጀምበር ችግኝ ተከላ ተፈጥሮን በማደስ የአርሶ አደሮችን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ፤ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት። ቡና እና አቮካዶን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰሜን ጎጃም ዞን መለያ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የሁሉም ልማታችን እና የሁሉም እድገታችን መሠረት አካባቢን መጠበቅ ነው ብለዋል። አካባቢውን የጠበቀ ማኅበረሰብ የግብርና ምርት እና ምርታማነቱን ያሳድጋል ነው ያሉት።
“መሬት የመኖራችን ምስጢር” ስለኾነች እንደ ልጅ በመንከባከብ ከአፈር መሸርሸር መከላከል እና ልጆቻችን ጤናማ በኾነ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
በተከላ መርሐ ግብሩ ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው ቄስ ልሳኑ ገብረ መስቀል እና አርሶ አደር አስማረ መኮንን ከዚህ ቀደም አካባቢያቸውን በአግባቡ ባለመጠበቃቸው ብዙ ቦታዎች በጎርፍ ክፉኛ መሸርሸራቸውን ተናግረዋል።
ይህን ከተገነዘቡ በኋላ በየዓመቱ ችግኝ መትከል መጀመራቸውን ነው የሚናገሩት። በአካባቢው ከሁለት ዓመት በፊት የተተከሉ ችግኞችም የተሸረሸሩ መሬቶችን እንዲያገግሙ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዕለቱ በጎርፍ ክፉኛ የተሸረሸረ መሬት ላይ ችግኝ በመተከሉ ደስተኛ መኾናቸውን ነው የነገሩን።
አርሶ አደሮቹ የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክበው እና ጠብቀው የተጎዳው መሬት እንዲያገግም እንደሚያደርጉም አረጋግጠውልናል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
