ለአካባቢ ጥበቃ እና ለምግብ ዋስትና ማረጋገጫ እየተተገበረ ያለ ሀገራዊ ግብ !

10
​በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ በኮሶ አምባ ቀበሌ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ንቅናቄ ተካሂዷል።
​የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ እታገኘሁ አዳሙ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥነ-ምሕዳርን ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ የሚገኝ ተግባር ነው ብለዋል።
​መርሐ ግብሩ ከሥነ-ምሕዳር ሽፋኑ ባሻገር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ዓላማ ያለው በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
​ተፈጥሮን ወደ ነበረችበት እንመልስ በሚል ርብርብ ሲደረግ ለችግራችን በጋራ መቆምን የምንለማመድበት ትልቅ ማኅበራዊ እሴት መኾኑን ነው የተናገሩት።
​የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ አሳግርት ወረዳ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለትውልድ የሚሻገር እና ተሞክሮ የሚወሰድበት አብርሆት ያለው ተግባር ማከናወኗን ገልጸዋል።
​ለዚህም የትጋት ውጤት የአካባቢው የልማት ገጽታ በራሱ ሕያው ምስክር መኾኑን ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ለትውልድ የሚቆይ ዘላቂ የልማት ሥራ መሥራት ስላለብን ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
​በዛሬው ዕለት ብቻ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ከ58 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመተከል ላይ እንደሚገኙም ገልጻዋል።
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያውያን በመተባበር ታሪክ መሥራት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት መርሐ ግብር ኾኖ ቀጥሏል።
Next article“መሬት የመኖራችን ምስጢር ነች”