“አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሰው ልጅን ከተፈጥሮ ጋር እያቆራኘ ነው”

3

 

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ በሚኾን መሬት ላይ ከ24 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአንድ ጀምበር እየተተከሉ ነው።

በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ወጣቶች፣ የመንግሥት
ሠራተኞች፣ የፈረሰኛ ማኅበር አባላት፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው አሻራቸውን አኑረዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሰው ልጅን ከተፈጥሮ ጋር እያቆራኘ መምጣቱን ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተተገበረው የአርንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢን ገጽታ በማሻሻል፤ የአፈር ለምነትን በመመለስ እና የደን ሽፋንን በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ቤዛዊት ጌታሁን በተራራዎች እና በወል መሬቶች ተወሰኖ የቆየው የችግኝ ተከላ የአርሶ አደሮችን ማሣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች ወደ ማልበስ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ችግኝ የመትከል እና ተንከባክቦ ለፍሬ ማብቃት የቆዬ ባሕል እንዳለው ያነሱት ኀላፊዋ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞችም ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

#AMECO #greenlegacy #Ethiopia

#እንጅባራ #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበአንድ ጀምበር እስከ አሁን ከ578 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መተከላቸውን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።
Next article«ዛሬ የማሳርፈው አሻራ የልጆቼን የነገ ሕይወት ብሩህ ያደርጋል» የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ