🌿🌱 “ዛሬ ችግኝ ብቻ አይደለም የምንተክለው ኢትዮጵያን የማጽናት ተስፋ ጭምር ነው” አቶ ጎሹ እንዳላማው

2

 

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጣና እና ዓባይ ተፋሰስ ኢኮሎጂን ለመጠበቅ እንዲሁም ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ ቀበሌ በታላቅ ንቅናቄ ተካሂዷል።

በዘንዘልማ ቀበሌ ገላድ ተፋሰስ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ዛሬ ችግኝ ብቻ አይደለም የምንተክለው ሰላምን፣ እድገትን እና ኢትዮጵያን የማጽናት ተስፋ ጭምር ነው ብለዋል።

ለዓባይ እና ጣና ተፋሰስ ቅርብ በመኾናችን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራችን ዋነኛ ትኩረታች ነው ሲሉም ገልጸዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። የፍራፍሬ እና የቡና ልማትን በክላስተር በማልማት ከተማችንን በምግብ ራስን የማስቻል ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መሠሉ ብርሃኑ በዛሬው ዕለት በሀገር ደረጃ 800 ሚሊዮን፤ በክልል ደረጃ ደግሞ ከ327 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአንድ ጀምበር እንደሚተከሉ ተናግረዋል። በገላድ ተፋሰስ ብቻ ከ338 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መመሪያ ኀላፊ የሰውዘር ደመላሽ እንደ ከተማ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከ20 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን እና የጽድቀት ምጣኔያቸውም 83 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። በዘንድሮው ዓመትም በዘጌ 100 ሄክታር የቡና ክላስተር፣ በወራሚት ቀበሌ 100 ሄክታር የአቮካዶ ልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ዋናው ዓላማም ምርቶችን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ እንደኾነ አብራርተዋል።

በመርሐግብሩ ችግኝ እየተከሉ ያገኘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም ለችግኝ ተከላው ከፍተኛ ፍላጎት እና ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የገላድ አካባቢ ቀደም ሲል በጎርፍ የተጠቃ እና አትክልት ያልነበረበት ነበር፤ አሁን ግን ከዚህ በፊት በጋራ ጥረት በተተከቱ ችግኞች ወደ አረንጓዴነት እየተቀየረ ይገኛል ብለዋል። ዛሬ የተተከሉ ችግኞች የነገ የሕይወታችን ተስፋ ናቸው ብለዋል ነዋሪዎቹ 🌳✨

#AMECO #greenlegacy #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ✍️ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“አረንጓዴ አሻራ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የጎላ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን
Next article“አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ለምግብ ዋስትናም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው” ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ.ር)