
በሀገር አቀፍ ደረጃ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በአንድ ጀምበር የ800 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን አረንጓዴ አሻራ የበለጸገች እና ለቀጣይ ትውልድ የምትመች ሀገርን ለመገንባት ትልቅ አቅም መኾኑን ጠቁመዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የጠፉ ሐይቆችን በመመለስ፣ ሥነ-ምኅዳርን በማሻሻል፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ ስኬት እና መነቃቃት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ በመኾኑ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።
ክልሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደመኾኑ ለልማት ሲባል የሚመነጠሩ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት አረንጓዴነታቸው የተጠበቀ፣ የተስተካከለ የአየር ንብረት እና የተሻለ የውኃ ሀብት ያላቸው አካባቢዎችን ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
