
ኢትዮ ቴሌኮም “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ መሳተፉን ገልጿል።
የዛሬው “የአንድ ጀንበር” የአረንጓዴ ልማት ሥራ በዘመናዊ ስትራቴጂ ተደግፎ ለዛሬውም ኾነ ለነገው ትውልድ ምቹ፣ ውብ እና ዘላቂ ሀገርን ለመገንባት በቁርጠኝነት የሚከናወን ታሪካዊ ተግባር መኾኑንም አስታውቋል።
የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ተቋሙ ለሚያለማቸው መሬቶች እና ችግኞች የእንክብካቤ ሥራዎች ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲኾን በቦታ ዝግጅት፣ በተከላ እና በእንክብካቤ ሂደት ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በዘንድሮው ስምንተኛ ዙር መርሐ ግብር ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ እንዲሁም በ18 ክልላዊ ዞኖች በሚገኙ መዳረሻዎቹ ዘመቻውን በተመሳሳይ ሰዓት እያከናወነ ሲኾን በዚህ ዙር ብቻ 250 ሺህ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
ለተከላ እና ለክትትል ሥራዎች 42 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበ ሲኾን ከ3ሺህ 500 በላይ ሠራተኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና መሪዎች በጋራ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በጉድጓድ ቁፋሮ፣ በችግኝ ማቅረብ እና በክትትል ሂደት ላይ ለተሰማሩ 2ሺህ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ኩባንያው በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 889 መዳረሻዎች ላይ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደተተከሉም ተጠቁሟል።
#AMECO #greenlegacy #Ethiopia
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ: ሀናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
