
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ800 ሚሊዮን “የአንድ ጀምበር” የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በጨለቃ ክላስተር በመገኘት አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ባለፉት ዓመታት ተፈጥሮን በአግባቡ ባለመጠቀማችን ለተፈጥሮ አደጋ ዳርጎን ቆይቷል ነው ያሉት። የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት ተዛብቶ ተፈጥሮ በማሸነፏ በአየር ንብረት ለውጥ የጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች እንዲደርሱ አድርጓል ብለዋል።
በሰዎች መካከል ያለው የተዛባ ግንኙነት በሽማግሌዎች በአጭር ጊዜ ሊፈታ ይችላል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተፈጥሮ እና የሰው የተዛባ ግንኙነትን ግን ለማስተካከል ረጅም ጊዜ ይወስዳል ነው ያሉት።
መንግሥት የተዛባውን ግንኙነት ለማስተካከል በአረንጓዴ አሻራ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል። መስማማት እና መታረቅ ብቻ ሳይኾን የሰዎችን ሕይወት የሚቀይሩ፤ አመጋገብን የሚያስተካክሉ፤ ለፋብሪካ ግብዓት የሚኾኑ፤ ንግድን የሚያሳልጡ፤ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያረጋግጡ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማቶች እየተስፋፉ መኾኑን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሀገርን ደን ከመራቆት፤ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማትን በማረጋገጥ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፤ የደረቁ ምንጮች እንዲጎለብቱ፤ የአየር ንብረት መዛባትን ተከትሎ የሚፈጠርን ወረርሽኝ እያስቀረ ይገኛል ነው ያሉት።
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት ዛሬ የምንሠራው ሥራ ለነገው ትውልድ መሠረት ነውም ብለዋል። ትናንት ባለመሥራታችን ማኅበረሰቡ በጤና እና በአመጋገብ ተጎድቶ ቆይቷል ነው ያሉት።
ይህንን ለመቅረፍ ችግኞችን በስፋት እየተከልን ነውም ብለዋል።
በክልሉ ከ1ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ እንደሚለማም ጠቁመዋል። 25 ሚሊዮን የቡና ችግኝ እንደሚተከልም ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ የደን ሃብትን ማሻሻል ብቻ ሳይኾን ለቤተሰብ ገቢ የሚፈጥር እና የሀገር ኢኮኖሚን የሚያሳድግ ነውም ብለዋል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት አመርቂ ውጤትን እያመጣ ይገኛልም ነው ያሉት። ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል። መትከል ብቻ ሳይኾን ጸድቀው ፍሬ እንዲያፈሩ እና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንዲኾኑ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
በክልሉ የደን ሽፋን ማደጉንም ገልጸዋል። ደቡብ ወሎ ዞን በደን ልማት ውጤታማ መኾኑንም ገልጸዋል። አካባቢው ለድርቅ ተጋላጭ እንደነበር አስታውሰው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የአፈር መሸርሸርን አስቀርቷል፤ የአፈር ለምነትን ብሎም ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
ሕዝቡ በግጭት ሳያሳብብ ልማት ላይ በትኩረት እየሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምታከናውነው ተግባር በአየር ንብረት ለውጥ ለሚቸገሩ ሀገራት እያስተማረች መኾኑንም አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ ለተገኙት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መሥመር ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በክልሉ የኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሥመር ወደ ሥራ እንዲመለስ በማድረጋቸው አመሥግነዋል።
አሻራቸውን ለማስቀመጥ በመምጣታቸውም አመሥግነዋል። ቃሉ የክልሉ የኢኮኖሚ ምንጭ ትኾናለችም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
