
እንግጫዬ ሰሌን ሳልደቁሰው ኩሌን … እያሉ ልጃ ገረዶች በእንግጫ ነቀላ በዓል ጊዜ ያዜማሉ።
ክረምቱ አብቅቶ አዲስ ዓመት ሲተካ በጎጃም አካባቢዎች ከሚከበሩ ደማቅ የባሕል እሴቶች መካከል የእንግጫ ነቀላ አንዱ ነው።
በዓሉ አሮጌው ዘመን ተጠናቅቆ የብርሃን እና የሰላም ዘመን መምጣቱን የሚያበስር ታላቅ የሕዝብ ትስስር መድረክ ነው። የልጃገረዶችም የነፃነት በዓል ነው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴት ልማት ባለሙያ በልስቲ ውቤ እንደገለጹት የእንግጫ ነቀላ በነሐሴ ወር ከፆመ ፍልሰታ ጀምሮ በዝግጅት ታጅቦ ከጳጉሜን 1 እስከ ጳጉሜን 5 የሚከበር የልጃገረዶች በዓል ነው ይላሉ። በዓሉ የልጃገረዶች መተጫጫም ነው።
በክረምት ወራት የለመለመው እንግጫ ፈንድቆ በአደይ አበባ እና በሶሪት አበባ ተውቦ ይጎነጎናል። ጨለማው ዘመን አልፎ የብርሃን ጊዜ መምጣቱን ከኖህ እርግብ ተምሳሌትነት ጋር በማያያዝም ይከበራል ነው ያሉት።
የበዓሉ ዝግጅት የሚጀምረው ልጃገረዶች ከጳጉሜን መጀመሪያ ላይ እንግጫ የሚነቅሉበትን ቦታ በመምረጥ ነው። ወጣቶችም ለችቦ (ለእሳት ማቀጣጠያ) የሚኾን እንጨት በመልቀም እና መገናኛ ቦታዎችን በማዘጋጀት ትብብር ያደርጋሉ።
በሰፈራቸው ተሠባሠበው ነጫጭ የክት ልብሶቻቸውን ለብሰው አምረው እና ተውበው ወደ ወንዝ ዳርቻ ወይም ለምለም መስኮች በዋዜማው የሚያመሩት ልጃገረዶች፣ እንግጫውን በደስታ እና በዜማ እየነቀሉ ያከማቻሉ።
ማምሻውንም ሴቶች ባሕላዊ ዜማዎችን እያዜሙ እንግጫውን ይጎነጉናሉ። ወንዶች ደግሞ ለቀጣዩ ቀን ብርሃን ማብሰሪያ የሚኾን ችቦ እና ዳቦት አብርተው ከልጃገረዶች ጋር አብረው ያመሻሉ።
በዕለቱ ማለዳ ልጃገረዶች የተዋበውን የእንግጫ ጉንጉን በአንገታቸው አጥልቀው ቤት ለቤት “እንኳን አደረሳችሁ” እያሉ በዜማ ያበስራሉ።
እንግጫውንም ወደሳሎን በመወርወር የቤቱ ባለቤቶች አንስተው ምሰሶው ላይ እንዲያስሩት ያደርጋሉ። በምላሹም ታላላቆች ዳቦ እና የተለያዩ ሥጦታዎችን ይሰጧቸዋል። ምርቃትም ይመርቃሉ።
ከሰዓት በኋላ ደግሞ ልጃገረዶች ወደ ቤተክርስቲያን በማምራት የእንግጫ ጉንጉን ያደርጋሉ። ወንዶችም ወደ ቤተክርስቲያን ያመራሉ ነው ያሉት። ከዚያም ልጃ ገረዶች እና ወጣቶች ከቤተክርስቲያን ክብ እየሠሩ የተለያዩ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ዜማዎችን ያዜማሉ።
በሂደቱ ወጣቶች ሎሚ በመወርወር የመረጧቸውን ልጃገረዶች የማሽኮርመም እና የትዳር አጋር የመምረጥ ሥርዓት ያከናውናሉ። ልጃገረዷም ከሌሎች ተለይታ ምልክት በማሳየት ፈቃደኛነቷን ትገልጻለች።
ይህ በዓል የልጃ ገረዶች እና የወጣቶች ትስስር፣ የማኅበረሰብ አንድነት እና የታላላቆች እና የታናናሾች ፍቅር የሚገለጽበት ድልድይ ኾኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል።
ይህንን ታላቅ ባሕላዊ እሴት አውዱን በመጠበቅ በደማቅ ኹኔታ ለማክበር መምሪያው በየወረዳው ከተጀመረው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን በፓናል ውይይት፣ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ እንዲሁም በባሕላዊ ኤግዚቢሽን ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች መደረጉም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
