
ኢትዮጵያውያን ዛሬም ዓለምን የሚያስደምም ታሪክ ለመጻፍ በየተራሮቹ፣ በየሜዳውና በየሸለቆው ተስፋን ለመትከል ለአረንጓዴ ልማት ማልደው ተሰልፈዋል።
ዛሬ የመሪን ጥሪ፣ የሀገርን አደራ ተቀብለን የምንተክለው የነገ ተስፋችንን ነው። ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከከተማ እስከ ገጠር የአንድ ጀንበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ንቅናቄን ጀምረዋል።
ይህ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ልማት ግባችን በትንሽ ጀምሮ በላቀ የመፈጸም፣ ጀምሮ የመጨረስ ብርቱ ሰልፋችን ማሳያ ሆኖ ቀጥሏል። የአረንጓዴ ትልማችን ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ፣ ትሩፋቱ ከእኛ አልፎ ለአጎራባች ሀገራትም እየተዳረሰ ይገኛል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ከምግብ ዋስትና እስከ ዘላቂ የደን ልማት አድማሱ የሰፋ ውጤትን እያመጣ፣ ትውልዱም ነገን እየተከለ፣ ሀገርን በላብና በዕውቀቱ እያጸና፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካን ተስፋ እየገነባ ነው።
ዛሬ ሁላችንም ክንዳችንን በማበርታት፣ የተራሮችን ገጽታ በአረንጓዴ ካባ እንሸፍናለን። የኢትዮጵያን ተፋሰሶች በለመለሙ ተክሎች እናለማለን። የችግኝ ተከላችንን ፀሐይ እስክትጠልቅ እንቀጥላለን።
ኢትዮጵያ ተስፋዋን ትተክላለች፤ ተስፋዋን ትንከባከባለች፤ ተስፋዋን እውን ታደርጋለች።
በርቱ እንበርታ!
