“የዘንድሮው የትኩረት አቅጣጫ ከመትከል ባለፈ መንከባከብ ላይ ማተኮር ይኖርበታል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

6

 

ኢትዮጵያ የ56 ቢሊዮን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ጉዞን ለማሳካት በዛሬው ዕለት የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር ተከላን እያከናወነች ትገኛለች።

በዕለቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ዳር ድንበሯን እና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ብትኾንም ለም አፈሯ እና የተፈጥሮ ሀብቷ በተለያዩ ምክንያቶች ሲመዘበር መቆየቱን አስታውሰዋል። የሀገሪቱ ዋነኛ ተስፋ ይህንን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ በመኾኑ “ኢትዮጵያ ተስፋዋን ትተክላለች፣ ትንከባከባለች፣ እውንም ታደርጋለች” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ተስፋን እንትከል” በሚለው መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተነሳሳው ሕዝባዊ ማዕበል እጅግ አስደናቂ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም ዕድሜ፣ የፖለቲካ አመለካከትም ኾነ የሥራ ሁኔታ ሳይገድበው፣ ከሕጻናት እስከ አዛውንት ድረስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተነስቶ የአረንጓዴ አሻራውን እያኖረ ይገኛል ነው ያሉት።

የዘንድሮው የትኩረት አቅጣጫ ከመትከል ባለፈ መንከባከብ ላይ ማነጣጠር እንደሚገባውም ጠቁመዋል። የችግኞቹን የጽድቀት መጠን ከ85 በመቶ በላይ ለማድረስ ከፍተኛ ክትትል እና እንክብካቤ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ጠቁመዋል።
በተጓዳኝም የተፈጥሮ ሀብት መታደስን በማረጋገጥ የጠፉ ምንጮች እና ሐይቆች እንዲያገግሙ፣ የዱር እንስሳት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እያደረገ ነው ብለዋል።

#AMECO #greenlegacy #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ተፈጥሮን ለማከም አግዟል።
Next articleስምንት ዓመታት፤ ቀጣይነት ባለው ተግባር!