የርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መልእክት፦

4
የምንተክላቸውን ችግኞች በመንከባከብና በመጠበቅ ለትውልድ አረንጓዴና ለምለም ምድር ማስተላለፍ ይገባል
በዛሬው እለት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 3 ቀበሌዎችን በሚያገናኘው የጨለቃ ክላስተር በመገኘት እንደ ሀገር እየተካሄደ በሚገኘው 8ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አሻራችንን አሳርፈናል።
በዚህ ክላስተር በተዘጋጀው 213.5 ሄክታር መሬት ከ60 ሽህ በላይ የማንጎ ችግኞች የሚተከሉ ይሆናል።
በክልላችን ደግሞ በ3 ሽህ 554 የተከላ ቦታዎች፣ በ65 ሽህ 900 ሄክታር መሬ 327 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ፤ በተከላውም 5.2 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ይህ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል የሚያልፍ ትርጉም ያለው ለትውልድ የሚተላለፍ የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የሁለንተናዊ ኃላፊነት መገለጫ ነው።
በተከታታይ ዓመታት ሲተገበር የቆየው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብስ በክልላችን የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በማገገም፣ የውሃና የአፈር ሀብትን በመጠበቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና ለልጆቻችን አረንጓዴና ዘላቂ አካባቢን ለማውረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ስለሆነም የአረንጓዴ አሻራ ስኬት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰቡ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአርሶ አደሮች፣ የግል ዘርፉ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው።
ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገው ሕይወት፣ የነገው ጥላ፣ የነገው ውሃ እና የነገው ተስፋ ነው። በመሆኑም የተከልነውን ችግኝ በመንከባከብና በመጠበቅ አረንጓዴና ለምለም ምድር በማስተላለፍ የትውልድ አደራችንን እንድንወጣ በራሴና በክልሉ መንግስት ስም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
Previous article“በባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል” ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ
Next article“በአንድ ጀምበር ተስፋን እና ለትውልድ ተሻጋሪ አረንጓዴ ኢትዮጵያን እናውርስ”