🍃 እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአረንጓዴ ልማት ባሻገር ለምግብ እና ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎችን እያለማ ነው።

15

 

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው አረንጓዴ ልማትን ከማስፋፋት ባለፈ የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ እና የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ሁለገብ ችግኞችን በማልማት ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር መልካም አባተ (ዶ.ር) ተቋሙ የግብርና እና አረንጓዴ ልማትን የልህቀት ማዕከል አድርጎ በመቅረጹ መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በየዓመቱ በችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ እንደ አንድ ባሕል ማዳበሩን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቻግኒ እና በራሱ ግቢ ውስጥ አራት የችግኝ ጣቢያዎችን አቋቁሞ አረንጓዴ ልማት ላይ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ችግኝ ጣቢዎች የደን እና ሀገር በቀል ዛፎች፣ የፍራፍሬ ተክሎች፣ የቅመማ ቅመም እና ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕጽዋት የሚለሙባቸው ናቸው ብለዋል። በችግኝ ጣቢያዎች በርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። በ2017/2018 ዓ.ም ለተከላ ከተዘጋጁ ከ163 ሺህ በላይ ችግኞች መካከል ከ59 ሺህ በላዩን ዩኒበርሲቲው መትከሉንም ጠቅሰዋል።

እንጅባራ እና አካባቢው ለአፕል ምርት ምቹ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ቀደም ሲል የአካባቢው አርሶአደሮች የአፕል ምርት ሲያመርቱ ያጋጥም የነበረውን በተባይ የመጠቃት ችግር መሠረት አድርገው ለዩኒቨርሲቲው ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ በሽታ የሚቋቋሙ የአፕል ዝርያዎችን እና የአየር ንብረቱን የሚቋቋሙ ተክሎችን ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

ችግኞች ለዩኒቨርሲቲው ውበት፣ ለሞዴል ተፋሰሶች ማገገሚያ፣ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭነት፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ለከተማው ማኅበረሰብ በዝቅተኛ ዋጋ እና በነፃ ተሰራጭተው እየተተከሉ እንደኾነም አመላክተዋል።

ከተተከሉ ችግኞች መካከልም ከ15 ሺህ በላይ የአፕል፣ የአቮካዶ እና ከጂማ መጥተው የተሻሻሉ የቡና ችግኞች በልዩ ጥንቃቄ የተተከሉ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለመድኃኒትነት በሚውሉ ዕጾዋት የተሸፈነ መኾኑንም አንስተዋል። በቀጣይም ከእነዚህ ዕጽዋት የኬሚካል ይዘቶችን በመቀመር ለፋርማሲ፣ ለሳሙና እና ለሎሽን ማምረቻነት ለመጠቀም መታቀዱን አመላክተዋል።

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአረንጓዴ ልማት ባሻገር ለምግብነት እና ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎችን በማልማት ተሞክሮ እያካበተ ነውም ብለዋል። ለቀጣናው አረንጓዴ ልማት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ እንደኾነ ገልጸዋል። ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ወረዳዎች የሚመጡ ጎብኝዎችም ዩኒቨርሲቲው ያከናወነውን የአረንጓዴ ልማት ተመልክተው ስለ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ያላቸው አመለካከት እንዲቀየር ማስቻሉን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚስማሙ የተሻሻሉ የአፕል እና የቡና ዝርያዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አርሶ አደሮችን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አጠናክተሮ እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት። ከተያዘው ክረምት ወቅት ቀደም ብሎ የአረንጓዴ ልማት ሥራ የጀመረ መኾኑን እና ነገ በሚከናወነው ሀገራዊ የችግኝ ተከላ መርሐግብርም ሚናውን እንደሚያስቀጥል አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለሠራው የአረጓዴ ልማት ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ቀደም ሲል ዕውቅና መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

#አሚኮ #እንጅባራ_ዩኒቨርሲቲ #GreenDevelopment

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ: ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“አፈሩ ሲጠረግ ተስፋዬም አብሮ ይጠረግ ነበር…”
Next article🌍 አረንጓዴው ዲፕሎማሲ – ድንበር ተሻጋሪው የኢትዮጵያ የሰላም እና የጋራ ብልጽግና አሻራ 🌱🤝