🌍 አረንጓዴው ዲፕሎማሲ – ድንበር ተሻጋሪው የኢትዮጵያ የሰላም እና የጋራ ብልጽግና አሻራ 🌱🤝

5

 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገራዊ የደን ሽፋንን ከማሳደግ እና ተፈጥሮን ከመታደግ አልፎ ሀገሪቱን በአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ላይ በአህጉሪቱ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ እና ታማኝነት ካላቸው ድምጾች አንዷ እንድትኾን አድርጓታል። ይህ በጥቂት ሀገራት ብቻ በሚታይ ግዙፍ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ላይ የተመሰረተ ስኬት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋና የለስላሳ ኅይል አካል እንድታደርግ አስችሏታል። ለዚህም ማሳያው አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ለጂቡቲ፣ ለናይጀሪያ፣ ለሩዋንዳ፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለሌሎችም ማካፈሏ ነው። ይህም በአፍሪካ ኅብረት፣ በኮፕ ጉባኤዎች እንዲሁም ከባህረ ሰላጤው እና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ባላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን እያስገኘላት እንደኾነ ከኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ይህ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ አቅጣጫ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ እና በበረሃማነት መስፋፋት ክፉኛ ለሚጠቃው የአፍሪካ ቀንድ እጅግ ወሳኝ ነው። ተፈጥሮ የሰው ሠራሽ ድንበር ስለማይገድባት በኢትዮጵያ የሚደረግ የደን ልማት ብቻውን የቀጣናውን ሥነ-ምኅዳር ሙሉ በሙሉ ሊታደግ አይችልም። በመኾኑም ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማጋራት የምሥራቅ አፍሪካን የአየር ንብረት ለመጠበቅ፣ የዝናብ ስርጭትን ለማስተካከል፣ የአፈር መሸርሸርን ለመግታት እና ተደጋጋሚ ድርቅን በጋራ ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው። ይህ የጋራ ሥነ-ምኅዳራዊ ጥበቃ ሀገራቱ ከተናጠል ጥረት ወጥተው ለቀጣናው ደኅንነት በጋራ እንዲቆሙ፣ እንዲሁም በፖለቲካዊ መድረክ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በማርገብ በጋራ ጠላታቸው (በድህነት እና በአየር ንብረት መዛባት) ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

ከሥነ-ምኅዳራዊው ፋይዳው ባሻገር ይህ ተግባር ድንበር ተሻጋሪ የጋራ ልማትን እውን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና አለው። የጋራ ተፋሰሶችን በመንከባከብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እና በሕዝቦች መካከል መተማመንን በመፍጠር ረገድ የተበረከቱት ችግኞች እንደ ዕውነተኛ የሰላም አምባሳደር ኾነው እያገለገሉ ነው። በጋራ ዛፍ መትከል የቀጣናውን ትስስር ከመሠረተ ልማት (እንደ መንገድ፣ ባቡር እና ኤሌክትሪክ) ባለፈ በተፈጥሮ ጭምር በማስተሳሰር የጋራ የነገ ዕጣ ፈንታን ከመጋራት ጋር እኩል ትርጉም የሚሰጠው የረጅም ዘመን ራዕይ ነው።

ይህንን የደን ልማት አመራር ከጠንካራ የማረጋገጫ መሠረተ ልማት ጋር ያጣመረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ አህጉራዊ የካርበን አሥተዳደር ማዕቀፎችን ለመቅረጽ የተሻለ ቦታ ላይ ትገኛለች። አፍሪካውያን በራሳቸው የተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚተገበሩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ላይ ውስን ተጽዕኖ ሲያሳድሩ የቆዩበትን ታሪክ በመቀየር አፍሪካ በአዳዲስ የዓለም አቀፍ አሥተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ሕግ ተቀባይ ሳትኾን ሕግ አውጭ እና አርቃቂ እንድትኾን ይህ ተግባር ሰፊ በር እንደከፈተላት የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። ይህ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በብዝኀ-ወገን መድረኮች በተከታታይ የሚያነሱት ሀገራዊ እና አህጉራዊ የስትራቴጂ ትልም አካል እንደኾነም አክሏል።

የተቀናጀ ጥረቱ ማሳረጊያ እና የዓለም አቀፍ ዕውቅና ማረጋገጫው ደግሞ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) በ80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ላይ በዘላቂ የደን አያያዝ ዘርፍ የተገኘው ታሪካዊ ሽልማት ነው። ይህ ዕውቅና ኢትዮጵያ በደን ሽፋን ፈጣን ዕድገት ያሳየችውን ተጨባጭ ልዕልና፣ በሕዝባዊ ንቅናቄ ያረጋገጠችውን የምግብ ዋስትና ትሩፋት እና ቀጣናውን ያስተሳሰረችበትን የላቀ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት አጉልቶ አሳይቷል። ሽልማቱ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት ጊዜያዊ ዘመቻ ሳይኾን ሀገርን ከጥፋት የመታደግ፣ አካባቢያዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና ለትውልድ ብሩህ ተስፋን የማውረስ ጥልቅ የሕልውና እና የልማት ራዕይ መኾኑን ለዓለም ሕዝብ በተጨባጭ ያስመሰከረ ደማቅ ድል ነው።

#አሚኮ #AMECO #አረንጓዴ_አሻራ #GreenLegacy #ኢትዮጵያ #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_27_2018_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🍃 እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአረንጓዴ ልማት ባሻገር ለምግብ እና ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎችን እያለማ ነው።
Next articleቻይና በአረንጓዴ ግንብ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ የምድርን ጤና ጠብቀዋል።