
በጋው አልፎ ክረምቱ ግም ሲል የደቡብ ወሎ የቃሉ ወጣገባ ኮረብታማ ቦታዎች በግብርና ልማት ላይ ሕይወታቸው ለተመሠረተ አርሶ አደሮች አጥፊ ተደርገው የሚታዩ ነበሩ። ከኮረብታማ ቦታዎች የሚነሳው ጎርፍ በዘር የተሸፈኑ ማሳዎችን ጠራርጎ በመውሰድ የአርሶ አደሮችን ድካም በየዓመቱ ከንቱ በማስቀረት አምርተው እንዳይጠቀሙ አድርጓቸው ቆይቷል።
የዚሁ ችግር ተጋላጭ የነበሩት የአበቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አሕመድ ሙሀመድ ከ10 ዓመታት በፊት ተራራዎች በመራቆታቸው ምክንያት ሰብላቸው በጎርፍ እየተወሰደ ኑሯቸውን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ተናግረዋል። አርሶ አደሩ እንደነገሩን በበጋ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ቢያከናውኑም፣ ግብዓት ተጠቅመው ሰብላቸውን ቢዘሩም የሚያገኙት ምርት ለቤተሰብ ፍጆታ በቂ ባለመኾኑ ምሳ በልተው እራት ለመድገም ይቸገሩ ነበር። በተለይ ደግሞ የኑሮ ውጣውረዱ በክረምት ወቅት ብሶ መሬቱም እህል ሲፈልግ የሚዘሩት እስከማጣት በመድረስ ለከፋ ችግር ይጋለጡ እንደነበር ተናግረዋል።
“መሬቱ ምርት አልባ ኾኖ ድህነቱ ሲከፋ፣ ቀዬየን ትቼ ወደ ከተማ ልሰደድ ወይስ ምን ላድርግ?” ብየ እጨነቅ ነበር ነው ያሉት አቶ አሕመድ ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
አርሶ አደር አሕመድ የነበሩበትን ሁኔታ በቁጭት በማስታወስ ለኑሯቸው መቀየር ብልሃቱ ችግኝ መትከላቸው መኾኑን አስረድተዋል። በአካባቢያቸው ባሉ የግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ትምህርት በዙሪያቸው የሚገኙ ኮረብታዎችን፣ የጎርፍ ሸንተረር ቦታዎችን እና ማሳቸውን ሳይቀር በጋራ እና በግል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች መትከል በመቻላቸው አሁን ላይ ያ! አስቸጋሪ የሕይወት ፈተና ታሪክ ኾኗል።
የቤተሰባቸው ኑሮ ተቀይሮ ከምግብ አልፎ በአትክልት እና ፍራፍሬ ሽያጭ (ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ…) በዓመት እስከ 500 ሺህ ብር ገቢ የሚያገኙበት ዕድል ተፈጥሯል። በተለይ ደግሞ በክላስተር ካለሙት የማንጎ ተክል ከአንድ እግር እስከ 15 ሺህ ብር ያገኛሉ። በቀጣይም ማንጎን ወደ ውጭ የመላክ ዕቅድ አላቸው።
“ጊዜው አሁን ነው፣ ዛሬ ያልተከለ ችግሩን ነገ መፍታት አይችልም” የሚሉት አርሶ አደር አሕመድ ለጎርፍ ተጋላጭ የኾኑ አካባቢዎችን ደግሞ በሀገር በቀል ችግኞች በመሸፈን ማሳቸው አገግሞ የሚያገኙትን የሰብል ምርትም በእጥፍ አሳድገዋል። አሁን ላይም አርሶአደር አሕመድ ኑሮቸው ከድህነት ወደ ዘመናዊነት የኑሮ ሥርዓት በመቀየሩ ደስተኛ እና ሠርተው የማይደክሙ ኾነዋል።
“አፈሩ ተጠራርጎ ሲሄድ ተስፋዬም አብሮ የተጠረገ ይመስለኝ ነበር፣ ለካስ ሁሉም መፍትሄ አለው” የሚሉት አርሶአደሩ በዚህ ዓመትም “ተስፋን እንትከል!” በሚለው የሀገራዊ የችግኝ ተከላ ጥሪ ተጨማሪ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ነግረውናል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ብቻ ከ1ነጥብ 5 እስከ 2 ቢሊዮን ቶን ለም አፈር በጎርፍ ይጠረጋል። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የችግኝ ተከላ ሥራዎችም ችግሩን በመቀነስ የምርት ብክነትን ከ30 እስከ 40 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ በግብርናው ዘርፍ የተጠኑ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የአረንጓዴ አሻራ ተግባርም ከገጠር እስከ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማሳተፉ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጫ መኾኑን ሲገልጹም”ዛሬ የምንተክላት እያንዳንዷ ችግኝ የነገዋን ኢትዮጵያ ምግብ፣ አየር እና ተስፋ የመስጠት አቅም አላት” ነው ያሉት።
በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመላው ኢትዮጵያ ሲተከሉ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ የዜጎችን ሕይወት መቀየር ዋና ግቡም ነው። ለዚህ ደግሞ የአርሶ አደር አሕመድ የሕይወት ተሞክሮ ማረጋገጫ ነው። ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም “ተስፋን እንትከል!” በሚል መሪ መልዕክት 800 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።
💬 እርስዎስ ምን ያህል ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጂተዋል? ሀሳብዎን በሀሳብ መስጫው ላይ ያካፍሉን!
#AMECO #GreenLegacy #የአረንጓዴ_አሻራ #የአካባቢ_ጥበቃ #GreenEthiopia #አርሶ_አደር
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ መላኩ ሙሉጌታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
