🎓”ሼል ፈጣሪ እንጂ ሼል ጠባቂ መኾን አይገባም ” ተመራቂዎች

8

 

የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ከ800 በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ እና በተለያዩ የሙያ ደረጃዎች አስመርቋል።
​
የኮሌጁ ዲን ፈለቀ ውቤ ኮሌጁ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለ28 ተከታታይ ዓመታት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሙያዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ እንዲገቡ ክትትል በማድረግ አምራች ዜጎችን እያፈራ መኾኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ መርሐ ግብሮችም በመጀመሪያ ዲግሪ እና በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ከ800 በላይ ሠልጣኞች ተመርቀዋል ነው ያሉት ። እነዚህ ተመራቂዎች በመደበኛ፣ በአጫጭር እንዲሁም በተግባር ሥልጠና የወሰዱ ብቁ ባለሙያዎች መኾናቸውን ነው የገለጹት ።

​ኮሌጁ ተመራቂዎችን በማስመረቅ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን፣ ከቀጣሪ አካላት ጋር የሥራ ትስስር የመፍጠር ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኅላፊ እና የኮሌጁ የቦርድ ሠብሣቢ ብርሃን ንጉሴ ተመራቂዎች የመንግሥት ቅጥር ሥራን ብቻ የሚጠብቁ ሳይኾኑ፣ በራሳቸው ጥረት የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። ሥራ ጠባቂ ብቻ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ዜጋ መኾን ይገባልም ነው ያሉት።

ተመራቂዎች በቀጣይ ሕይወታቸው በአካባቢያቸው ሰላምን በማስጠበቅ ለሌሎች ወጣቶች አርዓያ በመኾን ብሩህ የሀገር እንቁዎች መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የሀገርን ኢኮኖሚ ከፍ ማድረግ እና ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍቱ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ተመራቂ ዓለም ፀሐይ ጋሻው በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) የትምህርት ክፍል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ተመርቃለች። ተመራቂዋ የቀሰመችውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለሌሎችም ወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ትልቅ ዕቅድ እንዳላት ገልጻለች። ሕዝብን እና ሀገርን በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ መኾኗንም አረጋግጣለች።

ሌላኛው የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቀው ብርሃኑ እጅጉ ሥራ ፈጣሪ በመኾን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ለማበርከት ማቀዱን ተናግሯል።

#አሚኮ #BahirDarPolytechnic #Graduation2026 #TVETEthiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከአቮካዶ ልማት እስከ ኤክስፖርት ገበያ የአረንጓዴ አሻራ ገጸበረከት።
Next article“አፈሩ ሲጠረግ ተስፋዬም አብሮ ይጠረግ ነበር…”