
አርሶ አደር ናቸው፤ የሥራ ሰው ያውም የሥራ ወዳዱ
የሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ቆጋ አካባቢ ነዋሪ አርሶ አደር ሻረው በላይ። አርሶ አደሩ አርሰው እና አንደፋርሰው የሚያድሩ ንቁ አርሶ አደርም ናቸው። አርሶ አደሩ ባለፉት 7 ዓመታት በነበረው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በንቃት መሳተፋቸውን ይናገራሉ። የተከሉት የአቮካዶ ችግኝም አሁን ላይ አዙሮ እየከፈላቸው መኾኑን ተናግረዋል። መሬት እና ችግኝ የሚንከባከባቸውን ይወዳሉ መልሰውም ይከፍላሉ የሚሉት አርሶ አደሩ አሁን ላይ በጥረታቸው ልክ የአረንጓዴው አሻራ ዘመቻ እየጠቀማቸው መኾኑን ነግረውናል።
በአማራ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተሠራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በተለይም የአቮካዶ ምርት የሚሰጡ ችግኞች በስፋት መተከላቸው ዛሬ ላይ የተተከለው ችግኝ መልሶ እየከፈለ ይገኛል። ይህ ድንቅ ሥራ የኢኮኖሚ ተስፋዎችን ማብቀል ጀምሯል። ክልሉ ካለው ምቹ መሬት እና የአየር ንብረት ጸጋ ባሻገር የአቮካዶ ችግኞችን ተከሎ ከማምረት አንስቶ እስከ ውጭ ገበያ ትስስር ድረስ እየተከናወኑ ያሉ ሰፊ ሥራዎች ለአርሶ አደሮች የዕለት ተዕለት ድካም እፎይታን የሚሰጡ እና ሕይወቱን የሚቀይሩ ኾነው በተጨባጭ ታይተዋል።
የዚህ ተስፋ ሰጭ ጉዞ አንዱ ማሳያ አርሶ አደር ሻረው በላይ ናቸው። አርሶ አደሩ ቀደም ሲል በአካባቢያቸው አቮካዶ በብዛት ይመረት እንደነበር እና ኅብረት ሥራ ማኅበር ተቋቁሞም ምርቱ ለውጭ ገበያ ይቀርብ እንደነበር ያስታውሳሉ። ምንም እንኳ በተለያዩ ምክንያቶች ሂደቱ ተቋርጦ ቆይቶ የነበረ ቢኾንም፤ አሁን ላይ በአረንጓዴ አሻራ ገጸ በረከት ከግብርና ጽሕፈት ቤት በተገኘ እገዛ አቮካዶን በኩታገጠም የመትከል ሥራ በመሥራታቸው እየተጠቀሙ እንደኾነ እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ይህ የለውጥ ሂደት በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ አይደለም ባይ ናቸው የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ። በዞኑ ከሚተከሉ 1 ሚሊዮን የአትክልት እና ፍራፍሬ ተክሎች መካከል ቡና እና አቮካዶን በተለየ ሁኔታ በመትከል የዞኑ መታወቂያ ለማድረግ መሠራቱን ጠቁመዋል። ለዚህም ከ100 ሄክታር በላይ መሬት በአቮካዶ እና ከ100 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ለመሸፈን ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃም የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም ሥራ አሥኪያጅ ይበልጣል ወንድምነው እንደተናገሩት ፕሮግራሙ በአማራ ክልል 39 ወረዳዎችን እየደገፈ ይገኛል። በተያዘው ዓመትም በስድስት ወረዳዎች ላይ የተሟላ ድጋፍ በማድረግ በትላልቅ ኩታገጠሞች 950 ሄክታር መሬት በአቮካዶ ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተጠቅመው ምርታቸውን በሰፊው እንዲያመርቱ እና ያለምንም እንግልት በተሻለ ዋጋ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል ባይ ናቸው።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደሚሉት የአረንጓዴ ልማት ሥራ ውጤት እያመጣ ነው። በዚህ ሥራም ክልሉ አቮካዶን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ኾኗል ባይ ናቸው። አስር ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአቮካዶ ምርት ለኤክስፖርት ገበያ ዝግጁ መኾኑንም ነው የገለጹት። ምክትል ኀላፊው በቀጣይ ምርቱን አቀነባብሮ እስከ መላክ ድረስ ትልቅ እሳቤ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸው አረንጓዴ አሻራ ሀገርን እየጠቀመ በመኾኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
በክልሉ በርካታ አካባቢዎችም በተሠራው የረንጓዴ አሻራ ሥራ የአቮካዶ ልማት አርሶ አደሮችን ከድካም አላቆ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ እንደኾነም ጠቁመዋል።
#Ameco #GreenLegacy #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
