
በአማራ ክልል የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መፍትሄ ይዞ ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ችግር ተወያይተው ለመፍታት እየጣሩ እንደኾነ እንደሚገነዘቡ የተናገሩት አካል ጉዳተኞቹ በዚህ ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ በማሠባሠብ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የዋግ ኽምራ አካል ጉዳተኞች ማኅበር አባል ኪሮስ ገብረመስቀል እና ኪሮስ ፀሐዩ ሀገራዊ ምክክሩ አካታች እና ገለልተኛ ነው ብለዋል።
ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባለው የአጀንዳ አሠባሠብ ሂደት እና በውይይቱ አካል ጉዳተኞችም ስለ ሀገራቸው እንዲመክሩ ዕድል ያገኙበት ነው ብለዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ በምክክሩም ዕውነተኛ መፍትሔ ይገኛል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የዋግ ኽምራ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ምክትል ሠብሣቢ ጌትየ በየነ በበኩላቸው በሀገራዊ ጉዳይ ሁሉም ተሳታፊ መኾኑ ሁሉን አቀፍ መፍትሔ እንደሚያመጣ ነው የጠቆሙት።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ከታች ወደላይ አጀንዳ በጥንቃቄ እየሠበሠበ መሄዱ የአሠራሩን ፍትሐዊነት ያሳያል ያሉት ምክትል ሠብሣቢው ኢትዮጵያዊያን ለታሪክ የሚነገር ትልቅ መፍትሔ ያስቀምጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
#Ameco #EthiopianNationalDialogue #WagHemra
#ሰቆጣ #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋበ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
