“የብሔረሰቦች ቀን የሕዝቦችን መተዋወቅ እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታን በተግባር የምናሳይበት ታሪካዊ መድረክ ነው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

9
የ21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር መሪ ዕቅድ ውይይት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።
የውይይት መድረኩን የከፈቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በየዓመቱ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
21ኛው በዓል የሕዝቦችን መተዋወቅ እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተግባር የምናሳይበት ታሪካዊ መድረክ ነውም ብለዋል። ቀኑ ልዩ እና ታሪካዊ ትርጉም አለው ያሉት አፈ ጉባኤው 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ በማጠናቀቅ በአዲስ መንግሥት ምሥረታ ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አካሂዳ በውይይት ችግሮችን የመፍታት ዴሞክራሲያዊ ባሕልን የጀመረችበት ወቅት ነው፤ በምክክሩም በሕዝቦች መካከል መቀራረብን እና መተዋወቅ በተፈጠረበት ማግስት መከበሩ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
አፈ ጉባኤው በመልእክታቸው ያነሷቸው ዓበይት ጉዳዮች፦
✨ የዴሞክራሲ ጅምር
7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በሰላም በማጠናቀቅ በአዲስ መንግሥት ምሥረታ ማግስት የምናከብረው ታሪካዊ በዓል ነው።
🤝 የጋራ መግባባት 4ሺህ ሰዎች በአንድ መድረክ ተሠብሥበው በመሠረታዊ አጀንዳዎቻችን ላይ የተወያዩበትን ትልቅ ሀገራዊ ሁነት ይዘን መጥተናል።
🇪🇹 ኅብረ ብሔራዊነት በተግባር
በተጨባጭ በሕዝቦች መካከል አንድነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ሀገር መኾኗን አረጋግጠናል።
🌍 ብሔራዊ ጥቅም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እንደ መንግሥትም ኾነ እንደ ሕዝብ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል።
ባለፉት ዓመታት ያካበትነውን ልምድ እና ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች በማካፈል፣ በሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ጠንካራ አንድነት እንዲፈጠር በጋራ እንሥራ ብለዋል ዋና አፈ ጉባኤው።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article26 ቢሊዮን የአንድ ቀን ዶሮ ጫጩት ስርጭት በአማራ ክልል!