26 ቢሊዮን የአንድ ቀን ዶሮ ጫጩት ስርጭት በአማራ ክልል!

8
በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በተከናወኑ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በዶሮ እርባታ ዘርፍ ከተሰማሩት መካከል ወይዘሮ ጽላተማርያም ተመስገን በ50 ዶሮዎች የጀመሩትን ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ ሦሥት የማዕከላት ደረጃ በማሳደግ ለ137 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ድርጅታቸው የእንቁላል እና የዶሮ ስጋ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን መላክ የቻለ ሲኾን ለመጭው አዲስ ዓመትም 17 ሺህ ዶሮዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ከመንግሥት ሥራ በመውጣት በወተት ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩት የዘርፌ፣ ሀና እና ጓደኞቻቸው ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ሽመልስ አንጋው በበኩላቸው ሥራውን በ2 ላሞች እና በ40 ሺህ ብር ካፒታል ቢጀምሩም በአሁኑ ወቅት የላሞቻቸውን ቁጥር ከ20 በላይ፣ ካፒታላቸውንም እስከ 5 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ማኅበሩ በቀን 160 ሊትር ወተት ለከተማው ማኅበረሰብ የሚያቀርብ እና ለ15 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲኾን ከክልሉ ቢሮ በተገኘ ድጋፍ በቀን እስከ 30 ኩንታል መኖ የሚያቀነባብር ማሽን በመትከል የምርት መጠኑን ማሳደጉን ጠቁመዋል።
በድርጅቶቹ ውስጥ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ሰብለ ቸኮል እና አዲሴ ውበቱ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እያሥተዳደሩ እንደሚገኙ ገልጸው በቀጣይም በራሳቸው በዚሁ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ህልም ሰንቀው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሀብታሙ ዘገዬ በከተማዋ በቂ የወተት፣ የእንቁላል እና የስጋ አቅርቦት መኖሩን ገልጸው በዘርፉ ለተሰማሩ አልሚዎች የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት ከባንኮች ጋር እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሀብታሙ ሁነኛው በበኩላቸው በጎንደር ከተማ የተመዘገቡት ሥራዎች ተሞክሮ የሚኾኑ መኾናቸውን ገልጸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልል ደረጃ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን የወተት እና 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የእንቁላል ምርት ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል።
አቶ ሀብታሙ አክለውም በክልሉ 46 የመኖ ማቀነባበሪያዎች እንደሚገኙ እና በቀጣይም የአንድ ቀን ጫጩት ስርጭትን ወደ 26 ቢሊዮን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አደራጀው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዓለም ያልካደው የኢትዮጵያ ሐቅ በወንዞቿ ለዓለም ትተርፋለች፤ በባሕር በሯ ከዓለም ትገናኛለች።