
የታሪክ፣ የባሕል፣ የማንነት የደም ሥሮች፤ የመኖር እና የአለመኖር የሕልውና ምሽጎች፣ ከምንጫቸው እስከ መዳረሻቸው የኢትዮጵያውያንን የፅናት እና የነፃነት ተጋድሎ ይተርካሉ። በባሕል ውስጥ የሰላም እና የበረከት ምልክቶችም ናቸው። ለዘመናት ሀገርን ከጠላት የጠበቁ ተፈጥሯዊ ምሽጎችም ናቸው የኢትዮጵያ ወንዞች።
ተፈጥሮ ኢትዮጵያን ከማህፀኗ ፈልቀው ከራሷ አልፎ ዓለምን የሚያረሰርሱ ከ12 በላይ ወንዞች ባለቤት አድርጋታለች። እነዚህም ኢትዮጵያ የምትሰጥ እንጅ የምትቀበል ሀገር አለመኾኗን አጉልተው ይመሰክራሉ። በርግጥ “የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ” ለተሰኘችው ኢትዮጵያ ተፈጥሮ አድልታለች።
ኢትዮጵያ ለዘመናት እነዚህን ወንዞች ጠብቃለች። ከመጠበቅ ባለፈ አለመጠቀሟ አሳዛኙ ነገር ነበር። አሁን ሀገራዊ ዕይታው ተቀይሯል። የውኃ ሃብቷን በፍትሐዊነት በማልማት የሕዝቧን የኢኮኖሚ ነፃነት ለማረጋገጥ እና ድህነትን ለመቅበር እየሠራች ጉዞ ጀምራለች። ዓባይ ተገድቧል፤ ቀይ ባሕርም ይመለሳል። ከዓመት እስከ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ ጎረቤቶቿን ውኃ የምታጠጣው ኢትዮጵያ የራሷን የባሕር በር ማግኘቷ ፍትሐዊ ነውና።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “የኢትዮጵያውያን ታሪክ” እና “ዘ ኢትዮጵያን ቦርድላንድስ” በተሰኙት መጽሐፍታቸው ኢትዮጵያ በጥንት እና በመካከለኛው ዘመን በቀይ ባሕር ላይ የጸና አሥተዳደር እና ሉዓላዊነት የነበራት የባሕር ላይ ንጉሥ ነበረች በማለት ቀጣናውን በበላይነት ትመራ እንደነበር መስክረዋል። ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተገፍታ የባሕር በር አልባ የተደረገችው በተፈጥሮ ሳይኾን በፖለቲካ ሴራዎች እና በቅርብ ጊዜ ስሁት ውሳኔዎች መኾኑንም አረጋግጠዋል።
በፖለቲካ ሴራ እና ውዥንብር ከቀይ ባሕር የተገፋችው ኢትዮጵያ በርግጥ ሙሉ ኾና የተፈጠረች ሀገር ነበረች። የሚለማ አፈር እና ውኃ፤ የሚያለማ ጠንካራ የሰው ኃይል ኖሯት ነገር ግን ከቀይ ባሕር መገለሏ እጅጉን አጉድሏት ቆይቷል። ለዚህም ነው ወደ ቀይ ባሕር መመለስ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ትግል የሚኾነው።
ይህ ታሪካዊ ትግል ዓለም የማይክደው ሐቅ ነው። የኢትዮጵያ ከባሕር በር መገለል ኢ-ፍትሐዊ ነው፤ ወደ ባሕር በር የመመለስ መብት አላት በማለት የሚከራከሩላትም በዝተዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ዲፕሎማት ቲቦር ናጄ” የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከኢትዮጵያ ማሕፀን የሚፈልቁትን ወንዞች የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት ካላቸው፣ ኢትዮጵያም የራሷ ወደነበረው ተፈጥሯዊ ይዞታዋ ቀይ ባሕር የመመለስ እና የመጠቀም ሙሉ መብት አላት” በማለት “ስለ ቀይ ባሕር የመናገር እና የመወሰን መብት የባሕር ዳርቻው ሀገራት ብቻ ነው” የሚሉትን የግብጽ እና አጋሮቿን አፍ ማዘጋታቸው ይታወሳል።
ከ12 በላይ በኾኑ ወንዞቿ ዓለምን እያጠጣች ዘመናትን የተሻገረችው ኢትዮጵያ የሌሎችን መብት እያከበረች የራሷን የባሕር በር መብት የምትነፈግበት ምንም ዓይነት የሞራልም ኾነ የሕግ መሠረት አለመኖሩን ነው ያረጋገጡት።
ታዲያ ይህ ተፈጥሯዊ ችሮታዋ ተመልሶ የዕድገት ግቧን እንድታሳካ የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀይ ባሕር ሴረኞች ከሰጡት የልዩነት እና የመጠፋፋት አዙሪት ወጥቶ መልሕቁን ወደ ቀይ ባሕር ማዞር ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ወንዞችን በማልማት እና ወደ ቀይ ባሕር በመመለስ ወደ ሥልጣኔዋ እና ታላቅነቷ መመለሻ ጊዜው አሁን ነው።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
