በጥሩ ብርሃን መሠረታዊ ፖሊስ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የሠለጠኑ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ተመረቁ።

18

 

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጥሩ ብርሃን መሰረታዊ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ጥምር የፀጥታ ሀይሎችን አሠልጥኖ አስመርቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉን ሰላም የሚያውኩ ብረት ነካሽ ፅንፈኞችን ሕዝቡ እንደማይፈልጋቸው በምርጫ አረጋግጧል ብለዋል።

ወንበዴዎቹ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ላይ ታች ከሚሉ ባዕዳን ጋር ኀብረት ፈጥረው ግራ ቀኝ ቢሉም አይሳካላቸውም፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የዛሬ ተመራቂዎች ግን ለሀገር ዘብ በመኾን የወንበዴዎችን እና የህልማቸውን ግብዓተ መሬት ያፋጥናሉ ብለዋል።

ተመራቂ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም ዘቦች የሕዝብን የሰላም ማስከበር ሥራ ተረክባችሁ ሕዝብ ከመረጠው የመንግሥት መዋቅር ጋር በመቀናጀት ኅብረተሰቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት ኑሮውን እንዲመራ ግዳጃቸውን በብቃት እንዲወጡም አዛዡ አሳስበዋል።

“በባዕዳን ወረራ ጊዜ አርበኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ሀገራዊ ገድል እንደፈጸሙ ሀሉ፤ የዛሬ ተመራቂዎችም በሀገራችሁ፣ በሕዝባችሁና በዓላማችሁ ፀንታችሁ በመቆም የተጣለባችሁን ታሪካዊ ኀላፊነት እንድትወጡ አሳስባለሁ” ብለዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ተመራቂዎች የወስዱትን ሥልጠና በመጠቀም የቀጣናውን ብሎም የክልሉን እና የሀገርን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በማረገጋገጥ ሕዝቡ የተሟላ የሰላም አየር መተንፈስ እንዲችል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ተመራቂዎች እንደተናገሩት በቆይታቸው ተገቢውን ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርጉ፣ ወቅታዊ ሁኔታውን በሚገባ እንዲረዱ የተደረገበትና በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል የአመለካከትና የተግባር አንድነት እንዲፈጥሩ ተደርጓል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የምሥራቅ ዕዝ፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማሰልጠኛው አመራሮች እና አሠልጣኞች ተገኝተዋል።

ዘገባው የምስራቅ ዕዝ ነው።

#አሚኮ #defencenews #ethiopia

#ባሕርዳር ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌱 “ያለ ዛፍ ጥላ፣ ያለ ዕውቀት መላ የለም” ኢትዮጵያውያን
Next article“ሀገራዊ ምክክሩ ለችግሮች መፍትሄ ያመጣል ብለን ተስፋ ያደረግንበት ነው” የዋግኽምራ ነዋሪዎች